ሰሜንኮሪያ ሚሳኤል ያስወነጨፈችው በደቡብ ኮሪያ ላይ የኒውክሌር ጥቃት “የማስመሰል” ሙከራ መሆኑን ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, KCNA/REUTERS
ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ የጀመረችው የሚሳኤል ማስወንጨፎች በደቡብ ኮሪያ ላይ የኒውክሌር ጥቃት ማድረስን የሚመስል ሙከራ ነው ስትል ተናግራለች።
ይህ የተገለጸው ሰሜን ኮሪያ በአምስት ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያውን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኗን የስለላ ተቋማት ካስታወቁ በኋላ ነው።
በቅርቡ የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያ የጦር ልምምዶችን በጋራ አከናውነዋል።
ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ፒዮንግያንግ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ሰባት ሚሳኤሎችን አስወንጭፏል።
የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ሰኞ ዕለት እንደዘገቡት ሚሳኤሎቹ ታክቲካዊ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለመያዝ የተሠሩ ናቸው።
እነዚህ በጦር ሜዳ ጥቅም ላይ ለማዋል የታቀዱ አነስተኛ የአጭር ርቀት መሣሪያዎች ናቸው። ወታደሮቹ ሚሳኤሎቹ የእነዚህን አነስተኛ የኒውክሌር መሳይ አረሮች ማስታጠቅ ተለማምደዋል ብለዋል።
የደቡብ ኮሪያን ወታደራዊ ካምፖች፣ ወደቦች እና አየር ማረፊያዎችን በተሳካ ሁኔታ መምታት መቻሉን አስመስሎ ሙከራ መደረጉን አስታውቀዋል። ይህም ለአሜሪካ እና ለደቡብ ኮሪያ ማስጠንቀቂያ ነው ብለዋል።
መንግሥታዊው የዜና ወኪል ኬኤንሲኤ ባወጣው ዘገባ የሃገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ-ኡን ሙከራዎቹን ሲቆጣጠሩ እና "ሲመሩ" ያሳያሉ ያላቸውን ፎቶዎች አቅርቧል።
ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ከመጠቀም የምታገኘው ጥቅም የለም ያሉት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ-ዮል ናቸው።
"ሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር ማበልጸጓን በመቀጠል የኮሪያን ሪፐብሊክን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ስጋት ውስጥ እየከተተች ነው" ብለዋል።
"ኒውክሌር የጦር መሣሪያ ምንም ጥቅም እንደሌለው አምናለሁ።"
የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያ የስለላ ባለስልጣናት ከ2017 ወዲህ ሰሜን ለመጀመሪያ ጊዜ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራ በቅርቡ ልታደርግ እንደምትችል ሲጠቁሙ ቆይተዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜም ስትሞክር በነበረው ሚሳኤሎች ላይ የሚገጠሙ አነስተኛ ታክቲካዊ መሳሪያ ልትጠቀም እንደምትችል ባለሙያዎች ያምናሉ።
ባለፈው ወር ኪም ጆንግ ኡን ሃገራቸው ሰሜን ኮሪያን "የማይቀለበስ" የኒውክሌር ሃይል ባለቤት በማለት አውጀዋል። የኒውክሌር ጦር መሣሪያን የሚያደርጋትንም ሕግ አስቀድማ አውጥታለች። የቀድሞ ፖሊሲዋ ጥቃት ሲደርስ ብቻ ምላሽ ለመስጠት ነበር እነዚህን መሳሪያዎች እንድትጠቀም የሚፈቅደው።
በዚህ ዓመት የሚሳኤል ማስወንጨፍ ድግግሞሿንም ጨምራለች። ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ መልኩ በዚህ ዓመትም ከ40 በላይ ሚሳኤል አስወንጭፋለች።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከተወነጨፉት ሚሳኤሎች አብዛኛዎቹ ሰሜን ኮሪያ እና ጃፓን መካከል በሚገኝ ባህር ውስጥ ያረፉ የአጭር ርቀት ሚሳኤሎች ናቸው።
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ማክሰኞ ዕለት በጃፓን ድንበር ላይ ያቋረጠ የረዥም ርቀት ሚሳኤልም አስወንጭፋለች።
ተንታኞች በመሣሪያው ዲዛይን ላይ ተመስርተው እንዳስታወቁት አዲስ መካከለኛ ርቀት ያለው ባሌስቲክ ሚሳኤል ነው።
ሰሜን ኮሪያ በዚህ ዓመት ባቡሮች እና መኪኖችን ጨምሮ ከተለያዩ የማስወንጨፊያ ጣቢያዎች ሚሳኤሎች አስወንጭፋለች።
በሚንቀሳቀሱ አካላት መሳሪያዎቹ መገጠማቸው ለማጥቃት ፈታኝ ያደርጋቸዋል ሲሉ ተንታኞች ጠቁመዋል።
እነዚህ ሙከራዎች በአውሮፓውያኑ 2018 እና በ2019 መካከል ፒዮንግያንግ ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የኒውክሌር መሣሪያን በተመለከተ ድርድር ከጀመረች በኋላ የታየ ለውጥ ነው ተብሏል።
ተንታኞች እንደሚሉት ሰሜን ኮሪያ በግንቦት ወር ለተመረጡት እና ከሰሜን ኮሪያ ጋር በተያያዘ ጠንካራ አቋም ለሚያሳዩት እና ከአሜሪካ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ላላቸው የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ-ዮልም ምላሽ በመስጠት ላይ ነች።












