ጆ ባይደን እና ዢ ዢፒንግ በቀጣይ ሳምንት ሲገናኙ ምን ይነጋገራሉ?

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ዢፒንግ በቀጣይ ሳምንት ሳን ፍራንሲስኮ እንደሚገናኙ ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
ሁለቱ መሪዎች ኅዳር 5/2016 ዓ.ም. ነው ይገናኛሉ የተባለው። ባይደን ሥልጣን ከያዙ ለሁለተኛ ጊዜ ነው በአካል የሚገናኙነት።
ከእስራኤል-ሐማስ ጦርነት አንስቶ ስለ ታይዋን፣ ስለ ዩክሬን ጦርነት እና ስለተቀዛቀዘው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቻይና ሰላይ ፊኛ ልካለች ስትል አሜሪካ መክሰሷ፤ የቀድሞዋ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን መጎብኘታቸው ሌላው የአገራቱ ፍጥጫ ነው።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ባይደን ከቻይና ጋር ግንኙነት ለማደስ “ቁርጠኛ” ቢሆኑም ቻይና ግን “ዳተኛ” ናት ብለዋል።
“ፉክክሩን መቀነስ አንዱ ግብ ነው። ግጭት እንዳይነሳ ማድረግና ግንኙነት ማስቀጠልም ይገኝበታል” ብለዋል።
አሜሪካ የእስያ ፓስፊክ የምጣኔ ሀብት ትብብር ጉባዔ ሳንፍራንሲስኮ በምታዘጋጅበት ወቀት ነው መሪዎቹ የሚገናኙት።
ቻይና ግዛቴ ናት በምትለው ታይዋን ዙርያ መነጋገራቸው አይቀርም ተብሎ ይጠበቃል።
ታይዋን በቀጣይ ዓመት ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀች ነው።
የታይዋን ራስን የማስተዳደር ጥያቄን አሜሪካ እንዳትደግፍ ዢፒንግ ሊጠይቁ ይችላሉ።
ቻይና በታይዋን ድንበር የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንድትገታ ደግሞ የባይደን ጥያቄ ሊሆን ይችላል።
ቻይና በሳውዝ ቻይና እና ኢስት ቻይና ባሕር ያላት ጥያቄ፣ አሜሪካ ከቻይና የቴክኖሎጂ ግብዓት አለማስገባቷም የውይይት አጀንዳ ይሆናሉ።
ኢራን የእስራኤልና ሐማስን ጦርነት እንዳታባብስ ቻይና እንድትጠይቅ አሜሪካ ትሻለች።
ንግግራቸው ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል የሚለውን ላይ ተንታኞች ጥያቄ ቢያነሱም ግንኙነታቸውን ማደስ አንድ የሚጠበቅ ውጤት ነው።
አሜሪካ ቻይናን “እየከበበች፣ እያፈነችም ነው” ብላ ቻይና ትከሳለች።
በአሜሪካ የቻይና አምባሳደር ዢ ፌንግ ግንኙነት ለማደስ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን ከሰሞኑ ተናግረዋል።
ቻይና የምትፈልገው አሜሪካ “የቻይናን ሥርዓት ለመለወጥ እንዳትሞክርና ወደ ቀዝቃዛ ጦርነት እንዳይገባ ነው” ብለዋል።
ሰላዩ ፊኛ በአሜሪካ ሰማይ ላይ ከታየ በኋላ ነገሮች ተባብሰዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንከን የታቀደ ጉዞ እስከመሰረዝ ደርሰዋል።
በድጋሚ ለመጓዝ ከወሰኑ በኋላ ከዢፒንግ ጋር “ግልጽ ውይይት” መደጉን ተናግረዋል።
በአሜሪካ የሚካሄደው ጉባዔ ላይ ዢፒንግ በግላቸው ከነጋዴዎች ጋር ለእራት እንደሚገናኙ ተዘግቧል።
40 ሺህ ዶላር የሚከፍሉ እንግዶች ከቻይና ፕሬዝዳንት ጋር በአንድ ጠረጴዛ እንደሚቀመጡና እራቱ ላይ ለመገኘት ከ2 ሺህ ዶላር ጀምሮ ትኬት እንደሚሸጥ ተገልጿል።
የአሜሪካና ቻይና ግንኙነት ብሔራዊ ኮሚቴ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ይህ የእራት ሥነ ሥርዓት “ከፍተኛ” የቻይና ባለሥልጣናት የሚገኙበት እንደሆነ ቢገልጹም ዢፒንግ ስለመገኘታቸው አላረጋገጡም።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊት ጃኔት የለን ከቻይና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሂ ሊፌንግ ጋር ይገናኛሉ ተብሎም ይጠበቃል።
የቻይና ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን እንዳለው ጉብኝቱ በቻይና አሜሪካ መካከል ያለውን “መናቆር የሚገታ” እንዲሆን ባይደን ኃላፊነት አለባቸው ብሏል።
“በዋሽንግተን የአሜሪካና ቻይናን ግንኙነት ማጠልሸት የሚፈልጉ ጸለምተኛ ኃይሎች አሉ። ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በምላሹ መግታት ያሻል” ብሏል ዘገባው።












