የአንድ ኦስትሪያ ከተማ ነዋሪዎች በጎብኚዎች ተጨናነቅን ሲሉ ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ

ታትሟል

በኦስትሪያዋ ሆልስታት በተሰኘችው አነስተኛ ከተማ ነዋሪ የሆኑ በጎብኚዎች ተጨናነቅን በማለት ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣት መንገድ ዘጉ።

የዓለም ቅርስ ተብላ የተመዘገበችው ከተማ የነዋሪዎቿ ብዛት 700 ብቻ ቢሆንም በቀን እስከ 10 ሺህ ጎብኚዎችን ታስተናግዳለች።

በጎብኚዎች ቁጥር የተማረሩት ነዋሪዎች ወደ ከተማዋ መስህብ መዳረሻ የሚወስድ መንገድን በመዝጋት የዕለታዊ የጎብኚዎች ቁጥር እንዲገብ እና ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ጎብኚዎችን የሚያመላልሱ አውቶብሶች እንዲታገዱ ጠይቀዋል።

ቱሪዝም ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ቢሆንም ነዋሪዎች ግን የጎብኚዎቹ ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው ይላሉ።

በተራራማ ቦታ ላይ ማራኪ በሆኑ ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶች እና ሐይቆች የተከበበችው ከተማዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጎብኚዎች መዳረሻ ሆናለች።

ይህች አነስተኛ ከተማ በአንድ የደቡብ ኮሪያ የፍቅር ዘውግ ባለው ድራማ ላይ መታየቷ ዝናዋን ክፍ አድርጎት ቆይቷል። ሆልስታት በእስያ ባሉ አገራት እጅግ ዝነኛ ከመሆኗ የተነሳ በቻይና የዚህች አምሳያ ከተማ እየተገነባ ይገኛል።

በርካታ ጎብኚዎች ለኢንስታግራም ገጻቸው ሐይቅ፣ ጥንታዊ ቤቶች እና አናታቸው በበረዶ የተሸፈኑ ተራራዎች ከጀርባቸው አድርገው ሳቢ የሆኑ ‘ሰልፊዎችን’ ለመነሳት ወደ ከተማዋ ይጎርፋሉ።

ልክ እንደ የጣሊያኗ ቬኒስ ሁሉ በአውሮፓ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ጎብኚዎች ከሚጎበኙ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው ሆልስታት ነዋሪዎች ለደርሶ መልስ ጉብኝት በግዙፍ አውቶብሶች ታጭቀው በሚመጡ ነዋሪዎች ተሰላችተናል ይላሉ።

በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ላይ በጎብኚዎች እና በትራፊክ ፍሰት የተማረሩ ነዋሪዎች ሰዎች ‘ሰልፊ’ ለመነሳት በሚያዘወትሩት ቦታ እይታን የሚጋርድ ከእንጨት የተሰራ ግድግድ አቁመው ነበር።

ይሁን እንጂ ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰነዘረውን ቅሬታ ተከትሎ የተተከለው እንጨት እንዲነሳ ተደርጓል።

ከዚያ በኋላ የከተማዋ ከንቲባ ከተማዋን የሚያቋርጡ አውቶብሶች ቁጥርን በሲሶ ለመቀነስ አቅደው ነበር።

ሃልስታት ከተማ ከኮቪድ-19 ስርጭት በፊት በነበረው ዓመት 1ሚሊዮን ጎብኚዎችን አስተናግዳ ነበር።