በስፔን አንድ ሙሉ የገጠር መንደር ለገበያ ቀረበ

ሳልቶ ዴ ካስትሮ የገጠር መንደር በከፊል

የፎቶው ባለመብት, BALLES2601/WIKIMEDIA COMMONS

የምስሉ መግለጫ, ሳልቶ ዴ ካስትሮ የገጠር መንደር በከፊል
ታትሟል

በስፔን ሳልቶ ዲ ካስትሮ የሚባል አንድ የገጠር መንደር ለገበያ ቀርቧል። ደላሎችም ገዢ እያፈላለጉለት ነው።

ሳልቶ ዴ ካስትሮ በሰሜን ምዕራብ የሚገኝ ገጠራማ ትንሽ መንደር ነው።

ከፖርቹጋል ድንበር ጠጋ ብሎ ዛሞራ በሚባል አውራጃ የሚገኘው ይህ መንደር ዋጋው 259ሺህ ዶላር ይጠራል።

ይህ መንደር ከማድሪድ ከተማ የሦስት ሰዓት የመኪና መንገድ ነው።

መንደሩ ይህ ቀረሽ የሚባል አይደለም። በርካታ መኖርያ ቤቶች፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ትምህርት ቤት፣ ማዘጋጃ ቤት፣ መዋኛ፣ ሆቴል ያሟላ ነው። የጎደለው አንድ ነገር ነው፤ ነዋሪ።

በዚህ የገጠር መንደር ነዋሪ የለም።

ሳልቶ ዲ ካስትሮ መንደር ላለፉት 30 ዓመት ሰው ኖሮበት አያውቅም።

አንድ ባለጸጋ ይህን የገጠር መንደር በፈረንጆች 2000 ገዝተውት ነበር። ለቱሪስት ምቹ አደርገዋለሁ ብለውም እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር።

ይሁንና በአውሮፓ በወቅቱ የነበረው ቀውስ ሕልማቸውን አጨለመው።

ባለጸጋው ሆቴል ለመገንባትም የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠው ነበር፤ ዕቅዳቸው አልተተገበረም እንጂ።

ባለጸጋው 80ዎቹ ዕድሜ ላይ ሲሆኑ የገጠር መንደሩን የሚሸጡት እሳቸው የከተማ ነዋሪ ስለሆኑና እንዳሰቡት አካባቢውን መንከባከብ ባለመቻላቸው እንደሆነ ገልጠዋል።

ይህ የገጠር መንደር ለገበያ የቀረበበት የደላላ ድረ ገጽ እስከ አሁን 50ሺህ ሰዎች እንደጎበኙት ታውቋል።

300 ሰዎች ደግሞ የመግዛት ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

እነዚህም ከሩሲያ፣ ከፈረንሳይ ከቤልጂየም እና ዩናይትድ ኪንገደም ናቸው የመጡ ሰዎች ናቸው።

አንድ ስማቸው ያልተገለጸ ባለጸጋ ቀብድ ከፍለዋል ተብሏል።

ሳልቶ ዴ ካስትሮ በ1950ዎቹ በአንድ የኤሌክትሪክ ኩባንያ አማካኝነት ለሠራተኞቹ ቤት በመገንባት የተመሠረተ ገጠር ነው።

ነገር ግን ሠራተኞቹ የኤሌክትሪክ ዘርጋታ ሥራውን ሲጨርሱ ያንን ገጠር ለቀው ወጡ።

ከ1980ዎቹ ወዲህ ይህ ገጠር ነዋሪ አልባ ሆኖ ቀረ።

ይህ የገጠር መንደር ለገበያ ሲቀርብ ይህ የመጀመርያው አይደለም።

ከዚህ ቀደም በ6.5 ሚሊዮን ዩሮ ለገበያ ቀርቦ የነበረ ሲሆን ገዥ አጥቶ ቀርቷል።

አካባቢው የነበሩ ቁሳቁሶችም በሌሎች ተዘርፎ እንዲሁ ኦና ሆኖ ቀርቶ ነበር።

አሁን ጠቅላላ የገጠር መንደሩን ለመሸጥ የቀረበው ዋጋ በማድሪድ ወይም ባርሴሎና አንድ ቆንጆ ባለ አንድ መኝታ አፓርታማ መግዛት ቢችል ነው።