ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
200 ሺህ ብር ያወጣውን ሠንጋ የሸጡት አርሶ አደር ምን ይላሉ?
አቶ ኡስማን ሁሴን ከብቶችን እያደለቡ በመሸጥ ነው ሕይወታቸውን የሚመሩት።
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በሸነን ዱጎ ወረዳ የራያ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኡስማን ባለፈው ዓመት ሁለት በሬዎችን በ40 ሺህ እና በ50 ሺህ ብር መግዛታቸውን እና ማደለብ መጀመራቸውን ይናገራሉ።
በእርግጥ የሚያረቧቸው እንስሳት ቢኖሯቸውም ለገበያ በሚል ገዝተው ማደለብ የሁልጊዜም ሥራቸው ነው።
አቶ ኡስማን ሁሴን ለወራት ያደለቧቸውን ሁለት በሬዎች እያንዳንዳቸውን በ200 ሺህ እና በ150 ሺህ ብር መሸጣቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ኡስማን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ከዚህ ቀደም አደልበው ከሸጧቸው በሬዎች መካከል ይህንን ያህል ዋጋ ያወጣላቸው እንደሌለ ተናግረዋል።
“ከእኔ የገዛው ነጋዴ ነው። ሥራዬን እንዳደነቀው ነግሮኛል፤ ሽልማት ይገባሃል ሲል አድንቆኛል” ይላሉ አቶ ኡስማን።
አቶ ኡስማን ሁለቱንም ሠንጋዎች የገዛቸው አንድ ሰው መሆኑን ገልጸው፣ አትርፎ ለሌሎች መሸጡን እንደነገራቸውም ተናግረዋል።
“ደስ ብሎት ነው ይዞ የሄደው። አዲስ አበባ ወስዶ በተሻለ ዋጋ እንደሸጠው ደውሎ ነግሮኛል” ካሉ በኋላ በስንት እንደሸጠው ግን እንዳልነገራቸው አርሶ አደር ኡስማን ገልፀዋል።
አቶ ኡስማን የሚያረቧቸው ሌሎች እንስሳት ያሏቸው ሲሆን፣ በተጨማሪም በሬዎችን ገዝተው፣ እያደለቡ ይሸጣሉ።
አሁን የሸጧቸውን በሬዎች መስከረም ላይ 40 ሺህ እና 50 ሺህ ብር እንደገዟቸውና ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እጥፍ ትርፍ እንዳገኙ አስረድተዋል።
“በ200 ሺህ የሸጥኩት በ50 ሺህ የገዛሁት ነው። በ150 ሺህ የሸጥኩትን ደግሞ የገዛሁት 40 ሺህ ነው። ከዚህ ቀደም በዚህ ያህል ዋጋ ሸጬ አላውቅም።”
ከዚህ ቀደም በውድ ዋጋ ሸጥኩት የሚሉት በሬ ያወጣላቸው 80 ሺህ ብር መሆኑን የገለፁት አርሶ አደሩ፣ አሁን ኑሮ መወደዱ የበሬዎቹ ዋጋ እንዲጨምር ማድረጉን ይናገራሉ።
እነዚህን ሠንጋዎች በ60 ሺህ እና 80 ሺህ ሊሸጡ እንደነበር የተናገሩት አርሶ አደሩ፣ በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እና ምክር የተነሳ፣ አቆይተው በዚህን ያህል ዋጋ መሸጥ መቻላቸውን ገልፀዋል።
ሠንጋዎቹን ለማደለብ ምን ምን ይቀልቧቸዋል? ተብለው የተጠየቁት አርሶ አደር ኡስማን፣ “ምግብ እየቀያየርን ነው የምንሰጣቸው። ዛሬ የምንሰጣቸውን ነገ አንሰጣቸውም። በቆሎ ካስፈጨሁ በኋላ፣ በውሃ እንደ ገንፎ አርሼ እሰጣቸዋለሁ። በየ15 ቀኑ ክትትል ይደረግላቸዋል። የእንስሳት ሐኪምም ክትትል ያደርግላቸዋል” ሲሉ መልሰዋል።
አቶ ኡስማን አሁን ባገኙት ገንዘብ ተጨማሪ በሬዎች በመግዛት የማደለብ ሥራቸውን ማስፋት ያስባሉ።
የእንስሳት ዋጋ በኑሮ ውድነቱ የተነሳ መጨመሩን ገልፀው፣ እርሳቸው ከገዙበት እጥፍ በላይ አትርፈው መሸጥ መቻላቸውን ይናገራሉ።
“የእንስሳ ዋጋ ጨምሯል። እኔ ግን የልፋቴን ዋጋ ነው ያገኘሁት። በርካታ ሠንጋዎች አሉ። ግን ሁሉም ዋጋቸው መቶ ሺህም አያወጣም። የእኔ ከእነርሱ ውስጥ የተለየ ነው።”
የሚኖሩበት ዞን እና ወረዳ ኃላፊዎች እንዳበረታቷቸው እና ሊሸልሟቸው ማሰባቸውን አቶ ኡስማን ይናገራሉ።
ከዚህ በፊት የደለቡ በሬዎች በዚህ ዋጋ ተሽጠው ባያውቁም፣ በበዓላት ወቅት ግን እስከ መቶ ሺህ የተሸጡ በሬዎች መኖራቸው ተሰምቶ ያውቃል።