ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስምንት የእስራኤል ወታደሮች በራፋህ መገደላቸው ተነገረ
ትናንት ቅዳሜ ሰኔ 8/2016 ዓ.ም. በደቡባዊ ጋዛ በደረሰ ፍንዳታ ስምንት የእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን የአገሪቱ ጦር ገለጸ።
ከጥር ወር ወዲህ በጦርነቱ ወቅት በጦሩ ላይ ያጋጠመው አስከፊው ጉዳት ነው ተብሏል።
ወታደሮቹ በጦር ተሽከርካሪ ውስጥ እያሉ ከባድ ፍንዳታ እንደገጠማቸው ተገልጿል።
ፍንዳታው የደረሰው ባለፉት ሳምንታት የእስራኤል ኃይሎች ቁልፍ በሆነችው እና በራፋህ በምትገኘው ታል አል ሱልጣን አካባቢ ውስጥ በተደረገ ዘመቻ ነው።
የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ በበኩሉ የደፈጣ ጥቃት በማዘጋጀት ሮኬት ወደ ወታደራዊ ተሽከርካሪ መተኮሱን አስታውቆ ነበር።
ወታደሮቹ በራፋህ ታል አል ሱልጣን ካደረጉት ዘመቻ በመመለስ ላይ እያሉ መኪናቸው እንደጋየ ተገልጿል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ የእስራኤል ጦር 50 ተዋጊዎችን ገድለዋል። በጋዛ የሚገኘው እና በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር 30 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን አስታውቋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ከተገደሉት መካከል የ23 ዓመቱ ካፒቴን ዋሰም ማህሙድ አንዱ መሆኑን ገልጾ የሌሎቹ ወታደሮች ስም ለቤተሰቦቻቸው ካሳወቀ በኋላ ይፋ እንደሚሆን ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው እስራኤል “አገራችንን ለመከላከል ባደረግነው ፍትሃዊ ጦርነት ልብ የሚሰብር ዋጋ ከፍለናል” ብለዋል። “ህልውናችንን እና የወደፊት ህይወታችንን ለማረጋገጥ” ይህንን ጦርነት እንቀጥላለን ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት "እንዲህ አይነት ኪሳራ የሚፈጥረው ህመም እጅግ በጣም ብዙ ነው" ሲሉ ሃዘናቸውን ገልጸዋል::
የእስራኤል የምድር ጦር የሐማስን “የመጨረሻ ዋና ይዞታ” ብሎ ከጠራው ከራፋህ ለማስወጣት ጥቃቱን ቀጥሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ተጠልለውባታል በሚሉባት ራፋህ የሚደረግ ግጭት ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ እያስከተለ ነው ሲሉ የእርዳታ ድርጅቶች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጋዛ ህዝብ “አስከፊ ረሃብ እና ረሃብ መሰል ሁኔታዎችን” እየተጋፈጠ ነው።
የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ በርካታ የዓለም መሪዎች እስራኤል በራፋህ ሙሉ ወታደራዊ ጥቃት እንዳትፈጽም አሳስበዋል።
በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ37 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን እና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ቆስለዋል ወይም ተፈናቅለዋል ብሏል።
ጦርነቱ የጀመረው ሐማስ መስከረም 26 በእስራኤል ላይ ጥቃት በማድረስ ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደለ እና 251 ሰዎችን አግቶ ወደ ጋዛ ከወሰደ በኋላ ነው።