እንግሊዝ ከአለም ዋንጫ ውድድር ውጭ ስትሆን፣ ፈረንሳይ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈች

ታትሟል

ከፍተኛ ግምት የተሰጣት እንግሊዝ ከአለም ዋንጫ ውድድር ውጭ ሆነች።

በኳታሩ አልባይት ስታዲየም ከፈረንሳይ ጋር ትናንት ታህሳስ 1፣ 2015 ዓ.ም ባደረገችው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ እንግሊዝ ጥሩ እንቅስቃሴ ብታሳይም ወደቀጣዩ ዙር ለማለፍ ተስኗታል።

በተለይም የሃሪ ኬን ፍጹም ቅጣት ምት መሳት የእንግሊዝን መሸነፍ ያመላከተ ነበር።

ሃሪ ኬን በጨዋታው ላይ ስሪ ላየንስን እኩል ያደረገበትና ለእንግሊዝ 53 ጎሎች በማስቆጠር ክብረወሰን የያዘውን ዋይኒ ሩኒን የተስተካከለበትን ግብ በፍጹም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሎ ነበር።

ፈረንሳይ በ17ኛው ደቂቃ በኦሬሊየን ቹአሚኒ ጎል የመሪነቱን ስፍራ ተቆጣጥራ ነበር።

እንግሊዝ በጨዋታው የበላይነት ቢኖራትም የተሻሉ የጎል እድሎችን መፍጠር አልቻለችም።

 ኦሬሊዮን ቹአሚኒ በእንግሊዙ ተጫዋች ቡካዮ ሳካ ላይ ጥፋት በመፈጸሙ የተገኘችውንም የፍጹም ቅጣት ምት ሃሪ ኬን በመምታት ግብ በማስቆጠር እኩል መሆን ችለው ነበር።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ 12 ደቂቃ ሲቀረው አንትዋን ግሪዝማን ያሻገረለትን ኳስ ኦሊቪየር ጂሩድ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠራት ጎል ፈረንሳይ የመሪነቱን ቦታ ዳግም ተቆናጠጠች።

ሆኖም እንግሊዝ ባገኘችው የፍጹም ቅጣት ምት እኩል የምሆንበትን እድል ብታገኝም አባክናዋለች።

ፍጹም ቅጣት ምቱን የመታው ኬን ለሃገሩ ታሪክ ለማስመዝገብ እድሉን ቢያገኝም ነገር ግን ባልተለመደ መልኩን ኳሷን ወደላይ ጠልዟት ግቡን ስቷል።

በዚህም የእንግሊዝ የአለም ዋንጫ ግስጋሴና ህልም የተገታ ሲሆን ፈረንሳይ ወደቀጣዩ የግማሽ ፍጻሜም አልፋለች። በቀጣዩም ፈረንሳይ ከሞሮኮ ጋር የምትፋለም ይሆናል።

የሁለቱ አገራት ብሔራዊ ቡድኖች በተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን ከዓለም ዋንጫ ውጪ በጥሎ ማለፍ ግጥሚያ ሲገናኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በዓለም ዋንጫም ከአውሮፓውያኑ 1982 ወዲህ በጥሎ ማለፍ ውድድር የተገናኙት በዚህ ጨዋታ ነው።