ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ተጫዋች በክርኑ በመምታቱ በቀይ ካርድ ተሰናበተ
የአል-ናስር የፊት መስመር ተጫዋቹ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የተቃራኒ ክለብ ተጫዋች በክርኑ በመምታቱ ቀይ ካርድ ተሰጠው።
በሳዑዲ ሱፐር ካፕ የክሪስቲያኖ ሮናልዶ ቡድን አል-ናስር ከአል-ሂላል ጋር ለዋንጫ ለማለፍ ሰኞ ምሽት ባደረጉት ጨዋታ ነው ይህ የተፈጠረው።
የ39 ዓመቱ ሮናልዶ በ86ኛው ደቂቃ የአል-ሂላሉን አሊ አል ቡላሂ ደረት በክርኑ ከመታው በኋላ ተጫዋቹ ሜዳ ላይ መውደቁን ተከትሎ ዳኛው ቀጥታ ቀይ ካርድ አሳይተውታል።
ፖርቹጋላዊው ሮናልዶ ቀይ ካርድ ከተመለከተ በኋላ ዳኛውን ከጀርባ በቡጢ ሊነትራቸው አስቦ እጁን ከፍ ሲያደርግ ይታያል።
ሮናልዶ ታኅሣሥ 2022 ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቅንቶ አል-ናስርን ከተቀላቀለ በኋላ ቀይ ካርድ ሲመለከት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
አል-ናስር 2-0 እየተመሩ ሳለ ነው ሮናልዶ በቀይ ካርድ የወጣው። የቀድሞው የሊቨርፑል ተጫዋች ሳዲዮ ማኔ በጭማሪ ደቂቃ ለአል-ናስር አንድ የማስተዛዘኛ ጎል አስቆጥሯል።
ሶስት ጊዜ የሳዑዲ ሱፐር ካፕ አሸናፊዎቹ አል-ሂላል ሐሙስ ዕለት ዋንጫውን ለማንሳት አል-ኢቲሃድ ይፋለማሉ።
አል-ኢቲሀድ ሰኞ ዕለት በግማሽ ፍፃሜው አል-ዌህዳን 2-1 አሸንፈው ነው ለዋንጫ የደረሱት። የቀድሞው የሪያል ማድሪድ አምበል ካሪም ቤንዜማ እና የሞሮኮው አጥቂ አብድረዛቅ ሀምዳላህ ለኢቲሃድ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።
ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ቀጥታ ካርድ ከመመልከቱ በፊት ባጠፋው ጥፋት ቢጫ ካርድ ተመልክቶ ነበር።
ሮናልዶ ቀይ ካርድ ከመመልከቱ በፊት ግርግር ተነስቶ የሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች እርስ በርስ ሲፈታተጉ ታይተዋል።
ሮናልዶ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲሰናበት በለበጣ ለመሐል ዳኛው ሲያጨበጭብላቸው ተስተውሏል።
ፖርቹጋላዊው ኮከብ በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2022 ነው ወደ ሳዑዲው ክለብ አል-ናስር ያቀናው።
ሮናልዶ ከአል-ናስር በፊት ለእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ለጣልያኑ ጁቬንቱስ እና ለስፔኑ ሪያል ማድሪድ ተጫውቷል።