ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጋና ፕሬዚዳንት የአፍሪካ አገራት ክብርን ለማግኘት ምዕራባውያንን ሊለምኑ አይገባም አሉ
የአፍሪካ አገራት አለም አቀፋዊ ክብርን ለማግኘት እና ስለ አህጉሪቱ ያለውን ደካማ አመለካከት ለመቀየር ምዕራባውያንን ከመለመን ራሳቸውን ሊያላቅቁ ይገባል ሲሉ የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ-አዶ ተናገሩ።
"ልመናችንን አቁመን የአህጉሪቱን ሃብትና ጥሪት እዚሁ ከተጠቀምንበት እኛ አፍሪካውያን ከማንም ክብር መጠየቅ አይኖርብንም። የሚገባንን ክብር እናገኛለን ። አህጉሪቷንም መድረስ ወደምትችልበት ማበልጸግ ከቻልን ክብር ይከተላል" በማለት የጋናው ፕሬዚዳንት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት በዋሽንግተን ዲሲ የአሜሪካ- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በተከፈተበት ወቅት ነው።
ፕሬዚዳንት አኩፎ በጋራ ለማደግም በአፍሪካውያን መካከል የላቀ ትብብር እንዲኖር አሳስበዋል።
"አፍሪካውያን በሃገሮቻቸው ከሚኖሩበት በላቀ በሌሎች አህጉራት ላይ አይበገሬነትን አሳይተዋል። ለውጭው ዓለም እንደ ናይጄሪያዊ፣ ጋናዊ፣ ወይም ኬንያዊ ሳይሆን የጋራ ማንነታችንን፣ አፍሪካዊነትን መዘንጋት የለብንም። እንደ አህጉሪቷ ዜጎች እጣ ፈንታችን እርስ በርስ የተሳሰረ ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት አህጉሪቱ ክህሎት እና የሰው ሃይል ቢኖራትም የተቀናጀ የፖለቲካ ፍላጎትና ቀናነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የፕሬዚዳንቱ አኩፎ አዶ አስተያየት የተሰማው አገራቸው ያለችበትን የኢኮኖሚ ድቀት ለመቅረፍ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት በተስማማበት ቀን ነው።
በአህጉሪቱ የቻይና እና የሩሲያ ተጽእኖ እየጨመረ በመምጣቱ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ከአሜሪካ ጋር በትብብር ለመስራት በዋሽንግተን ይገኛሉ።
የ49 አገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ሁለተኛው የአሜሪካ- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ታኅሣሥ 04/2015 ዓ.ም. ተጀምሯል።
ከማክሰኞ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ዓለማችንን እየፈተኗት ያሉ ተግዳሮቶች የአየር ንብረት ቀውስ፣ መልካም አስተዳደር፣ የምግብ ዋስትና እና የዓለም ጤናን የሚጨምር ሲሆን፣ እንዲሁም የአሜሪካ-አፍሪካ የንግድ እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማጠናከር ላይ ያተኩራል።
በጉባኤው ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቡድን 20 ውስጥ የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ቦታ እንዲያገኝ ድጋፍ እንደሚሰጡ ይጠበቃል ተብሏል።