ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞ የፓኪስታን ፕሬዝዳንት ፐርቬዝ ሙሻራፍ በ79 ዓመታቸው አረፉ
የቀድሞ የፓኪስታን ፕሬዝዳንት የነበሩት ፐርቬዝ ሙሻራፍ በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ሙሻራፍ በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች መዳረሻ በሆነችው ዱባይ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ነው የእረፍታቸው ዜና ዛሬ የተሰማው።
ሙሻራፍ ባለ አራት ኮከብ ጄኔራል የነበሩ ሲሆን ደም ባላፋሰሰ መፈንቅለ መንግሥት እንደ አውሮፓዊያኑ በ1999 ሥልጣን ከያዙ በኋላ 10 ዓመት ለሚጠጋ ዘመን ፓኪስታንን መርተዋል።
ጀኔራል ሙሻራፍ በወታደሩ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው፣ ሰልፍ አሳማሪ፣ ከእነ በትረ መኮንናቸው ወታደራዊ አለባበስ የሚያውቁ፣ ጥንቁቅ እና ንቁ ጀኔራል ነበሩ ይባልላቸዋል።
በአገራቸው ሕዝብ ዘንድ ጥርስ ውስጥ ያስገባቸው ደግሞ አሜሪካ መራሹን የጸረ ኢስላማዊ አክራሪዎችን ዘመቻም ተቀብለው በማስፈጸማቸው ነበር።
ሙሻራፍ እምብዛምም ባልተለደና የሰውነት ክፍሎችን በሚጎዳ አሚሎይዶሲስ በሚባል በሽታ ሲሰቃዩ ነበር።
ለረዥም ጊዜም የአልጋ ቁራኛ የነበሩ ሲሆን በተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቼር) ነበር የሚንቀሳቀሱት።
የፓኪስታን መከላከያ ሚኒስትር በመገናኛ ብዙኃን ባስተላለፈው አጭር መልእክት “ለሙሻራፍ አላህ ምሕረቱን ይስጣቸው፤ ለቤተሰባቸውም መጽናናትን እንመኛለን” ብሏል።
ሙሻራፍ የቀድሞ የኮማንዶ አባል ሲሆኑ የተሳካ የሚባል መፈንቅለ መንግሥት ከመሩ በኋላ ፓኪስታንን በአስቸጋሪ ወቅት የመሩ ፖለቲከኛ ናቸው።
ፓኪስታን ከሕንድ በ1947 ከተለየች በኋላ በርካታ መፈንቅለ መንግሥት አስተናግዳለች። ሙሻራፍ የገለበጡት የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍን ነበር።
ኒክሊየር ታጣቂዋን ፓኪስታንን በከፍተኛ ውዝግብ የመሩት ሙሻራፍ ከሕንድ ጋር ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡበት ወቅትም ነበር።
በመጨረሻም በ2008 ከሥልጣን የወረዱት ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ ነው።
ሙሻራፍ አገራቸው በአሸባሪዎችና አክራሪዎች በምትናጥበት ወቅት አገራቸውን ያገለገሉ መሪ ሲሆኑ ከበርካታ የግድያ ሙከራዎችም አምልጠዋል።
የሙሻራፍ ፓርቲ ከ2010 ጀምሮ በምርጫ ቢወዳደርም የተሳካለት አልሆነም።
ሙሻራፍ በ2019 በሌሉበት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበረ ሲሆን ከወር በኋላ ይህ ፍርድ ተቀልብሷል።
በመጨረሻም የአገር ክህደት ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ በስደት ወደ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ በማቅናት በዚያው ሕይወታቸው አልፏል።