በአሜሪካው የካፒቶል ሂል አመፅ ላይ የተገደለችው ግለሰብ ቤተሰቦች 5 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ተከፈላቸው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአውሮፓውያኑ 2021 በአሜሪካ ኮንግረስ በተነሳው አመፅ ላይ ስትሳተፍ የተገደለችው ግለሰብ ቤተሰቦች 5 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ሊከፈላቸው ነው።

የትራምፕ አስተዳደር የቀድሞ የአሜሪካ አየር ኃይል አባል ለሆነችው አሽሊ ባቢት ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።

የካፒቶል ፖሊስ ኃላፊ ቶም ማንጀር በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ "በውሳኔ እጅግ ተበሳጭቻለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

ግለሰቧን ገድሏል የተባለው የካፒቶል ሂል ፖሊስ መኮንን ጥፋት አልፈፀመም ተብሎ ነፃ ወጥቷል።

የባቢት ቤተሰብ እና ወግ አጥባቂው ጁዲሻል ዎች የተሰኘው ድርጅት ናቸው መንግሥት 30 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍላቸው ክስ ያቀረቡት።

በአውሮፓውያኑ ጥር 6፣ 2021 በሺዎች የሚቆጠሩ የፕሬዝደንት ትራምፕ ደጋፊዎች ወደ ካፒቶል ሂል በማምራት የአሜሪካ ኮንግረስን ጥሰው መግባታቸው ይታወሳል።

አመፀኞቹ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ምርጫ ማሸነፋቸውን የሚያበስረው ወረቀት ላይ ፊርማ እንዳይፈረም ለማድረግ ነው አመፅ የቀሰቀሱት።

የሕዝብ እንደራሴዎች ሰርተፊተኬቱ ላይ ፊርማ ለማሳረፍ ተሰባስበው በነበረበት ወቅት ነው አመፀኞቹ በኃይል ወደ ሕንፃው ያመሩት። በርካታ የሕዝብ እንደራሴዎች ለደኅንነታቸው በመስጋት አካባቢውን ጥለው ሸሽተዋል።

ባቢት ከአመፀኞቹ መካከል ስትሆን በር ገንጥላ ለመግባት ስትሞክር ትከሻዋ አካባቢ በጥይት ተመትታ ስትወድቅ የሚያሳይ ቪድዮ ተለቋል። ግለሰቧ ወደ ሆስፒታል ብትወሰድም ልትተርፍ አልቻለችም።

የባቢት ቤተሰቦች የፖሊስ መኮንኑ የፈፀመው ድርጊት ኃላፊነት የጎደለው ነው፤ ባቢት በጥይት ተመትታ ስትወድቅ እጇ አየር ላይ ነበር ሲሉ ተከራክረዋል።

የቤተሰቡ አባላት እንደሚሉት ባቢት በአመፁ የተሳተፈችው ትራምፕ የ2020 የአሜሪካ ምርጫ ተጨበርብሯል ማለታቸውን ተከትሎ ነው። ምርጫው ስለመጨበርበሩ የሚጠቁም ምንም ዓይነት ማስረጃ አልተገኘም።

የፖሊስ መኮንኑ ማይክል ቢርድ ተኩስ የከፈተው ሕግ አውጭዎች አደጋ ላይ መሆናቸውን ተከትሎ እንደሆነ ተናግሮ ነበር።

የካፒቶል ፖሊስ ባደረገው ምርመራ የመኮንኑ ውሳኔ ሕይወት የታደገ እንዲሁም የፖሊስን ሥልጠናና እና አካሄድ የተከተለ ነው ብሏል። የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴርም ምርመራ አድርጎ ጥፋተኛ አይደለም ማለቱ ይታወሳል።

ባለፈው ጥር ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጣን የጨበጡት ዶናልድ ትራምፕ 1500 ገደማ ለሚሆኑ የካፒቶል ሂል አመፅ ተሳታፊዎች ምሕረት አድርገዋል። ምሕረት ከተደረገላቸው መካከል ፖሊስ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ይገኛሉ።

ትራምፕ አክለው የካፒቶል ሂል አመፅን ሲመለከቱ የነበሩ የፌዴራል መርማሪዎችን ማባረራቸው አይዘነጋም።

ባለፈው መጋቢት ኒውስ ማክስ ከተሰኘው ወግ አጥባቂ የተሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቆይታ የነበራቸው ትራምፕ "የአሽሊ ባቢት ትልቅ አድናቂ" መሆናቸውን ጠቅሰው "ምንም ጥፋት ሳትፈፅም በቆመችበት" ነው የተተኮሰባት ብለዋል።