ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዴሞክራቲክ ኮንጎ ከእስር ቤት ለማምለጥ በተደረገ ጥረት የ129 እስረኞች ሕይወት አለፈ
በዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ ከሚገኘው ትልቁ እስር ቤት ለማምለጥ በተደረገ ጥረት የ129 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጃክሜይን ሻባኒ 24 ታራሚዎች በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው ማለፉን የተቀሩት ግን ለማምለጥ በተደረገ ጥረት ተረጋግጠው እና ታፍነው መሞታቸውን ተናግረዋል።
ይህ በአገሪቱ ትልቁ እና ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት ማካላ እስረቤት ከ7 ዓመታት በፊት 4ሺህ የሚሆኑ እስረኞች አምልጠው ነበር።
የአካባቢው ነዋሪዎች ሰኞ ዕለት ከእኩለ ለሊት በኋላ ከማረሚያ ቤቱ አቅራቢያ በርካታ የተኩስ ድምጽ መስማታቸውን ተናግረዋል።
“ከለሊቱ 7 ሰዓት እስከ ንጋት 11 ሰዓት አካባቢ ድረስ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር” በማለት የአካባቢው ነዋሪ የሆነው ዳዲ ሶሶ ለኤኤፍፒ ተናግሯል።
ይህ ነዋሪ ከእስር ቤቱ ውጪ በጥይት ተመትተው የተገደሉ ታራሚዎችን አስክሬን ፖሊስ ሲያነሳ መመልከቱን ተናግሮ ያመለጡ እስረኞችም መኖራቸውን ገልጿል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሻባኒ ከሞቱት 129 ሰዎች በተጨማሪ ወደ 60 የሚጠጉ ታራሚዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ በፖሊስ አባላት ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ያሉት ነገር የለም።
“የደኅንነት ኃይሎች፣ ፖሊስ እና የአገሪቱ ጦር እስረኞች እንዳያመልጡ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰዳቸው ሊደነቁ ይገባል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከእስር ቤት ለማምለጥ በተደረገው ጥረት የማዕከላዊ እስር ቤቱ የአስተዳደር ሕንጻዎች በእሳት መያያዛቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
በ1950ዎቹ የተገነባው ማካላ እስር ቤት 1ሺ 500 እስረኞችን የመያዝ አቅም ቢኖረውም ከ14ሺህ በላይ ታራሚዎች ይዞ እንደሚገኝ ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ከአራት ዓመታት በፊት በዚህ እስር ቤት ባለው የምግብ እጥረት እና የንጽህና ጉድለት ታራሚዎች ሕይወታቸው እያለፈ እንደሆነ ዘገባ ሰርቶ ነበር።
ከአቅሙ በላይ ታራሚዎችን በያዘው እስር ቤት የተፈጠረው ምን እንደሆነ ዓለም አቀፍ ገለልተኛ ተቋም ምርምራ እንዲያደርግ የመብት ተሟጋቾች እየጠየቁ ይገኛሉ።