አወዛጋቢው ናይጄርያዊ ፓስተር ከዩናይትድ ኪንግደም ሊባረር መሆኑን አስተባበለ

ናይጄሪያዊው ታዋቂ ፓስተር፣ ቶቢ አዴግቦዬጋ፣ ቤተ እምነቱ በገንዘብ አያያዝ ላይ ውንጀላ ከቀረበበት ዩናይትድ ኪንግደም ሊባረር ነው የሚለውን መረጃ ውድቅ አደረገ።
በአሁኑ ጊዜ ኔሽን ፋሚሊ በመባል የሚታወቀው እና ቀድሞ ኤስፒኤሲ ኔሽን (Salvation Proclaimer Ministries Limited) ይባል የነበረው ቤተ እምነት መሪ የሆነውት ፓስተር አዲግቦዬጋ ለቢቢሲ እንደተናገረው "ከአገር እንድባረር የተላለፈ ትእዛዝ የለም፤ ይህንን ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ" ብሏል።
የፍርድ ቤቱ ጉዳይ አሁንም "በሂደት ላይ ያለ ነው" ሲሉ አክሏል
በውድ ጌጣ ጌጦች ተንቆጥቁጦ፣ የሉዊ ቩቶን ከረባት አስሮ ወንጌል የሚሰብከው ይህ ፓስተር የ25 ዓመት ወጣት እያለ በ2005 ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በጎብኚ ቪዛ መግባቱን እና ቤተሰቦቹ የኢሚግሬሽን ወረቀቶቹን ይጨርሳሉ ብሎ ገምቶ እነደነበር ይናገራል።
የሆነው ግን ይህ አልነበረም።
የኢሚግሬሽን ሁኔታውን ለማስተካከል አስር ዓመታት የሚጠጋ ጊዜ መዘግየቱን በመጥቀስ "ተዘናጋሁኝ" ብሏል።
አክሎም ከተባረረ በኋላ ቤተ እምነቱን ወደ ናይጄሪያ ለማዛወር እንደሚቸገርም ገልጿል።
በታኅሣሥ ወር የዩኬ በጎ አድራጎት ኮሚሽን ባደረገው ምርመራ በቤተ እምነቱ ውስጥ "ከባድ የሥነ ምግባር እና/ወይም የአስተዳደር ጉድለት" አግኝቷል።
ነገር ግን ፓስተር አዴግቦዬጋ እነዚህን ውንጀላዎች ውድቅ አድርጓል።
"ውሸት ነው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ላለፉት አራት ዓመታት ክትትል ሲያደርጉ ነበር" ብሏል።
ይህ ቤተ እምነቷ ያጋጠማት የመጀመሪያው ክስ አይደለም።
እ.ኤ.አ. በ2019 የቢቢሲ ፓናሮማ የምርመራ ዘገባ ወጣት የጉባዔው አባላት የገንዘብ ብዝበዛ እንደሚደርስባቸው አሳይቷል።
አባላቱ የግል ስራቸውን ለመጀመር ከወሰዱት ብድር ለቤተ እምነቱ እንዲለግሱ እንደሚገደዱ ተናግረዋል።
ቤተ እምነቷም ሆነች ፓስተር አዴግቦዬጋም በወቅቱ እነዚህን ውንጀላዎች ውድቅ አድርገዋል።
"በአንድ ቦታ 1,000 ሰው ካለህ 30 ሰው አይከፋም ልትለኝ ትችላለህ? እንዴት ማንንም ሳታስከፋ ድርጅት ልትመራ ትችላለህ?" በማለት ተናግሯል።
የክርስቲያን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን በዩናይትድ ኪንግደም እንደ በጎ አድራጎት ድርጅት በ 2012 ተመዝግቦ የተጀመረ ሲሆን፣ ተጋላጭ ሰዎችን ለመርዳት፣ የጦር መሳርያ ጥቃትን ለመቅረፍ እና ወጣት አጥፊዎችን ለመርዳት በሚል የተቋቋመ ነበር።
ፓስተር አዴግቦዬጋ ቤተ እምነቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ለጥቃት ሊውሉ ይችሉ የነበሩ ቢላዎችን ከጎዳናዎች ላይ በማስወገድ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች።
"አንድን ማህበረሰብ ለመርዳት፣ ከዝቅተኛ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ዳራ የሚወጡ ወጣቶችን ከወንጀል በማውጣት ተግባራዊ እርምጃ እናምናለን።"
ፓስተር አዴግቦዬጋ በተቀናጣው አኗኗሩ፣ በዲዛይነር በሚሰፉት ልብሶቹ፣ በውድ ጌጣጌጦቹ እና በውድ ሰዓቶቹ ላይ የሚሰነዘረውን ትችትም በተመለከተ አስተያየቱን ሰጥቷል።
በማዕከላዊ ለንደን የሚገኘው የቢቢሲ ቢሮ ሲመጣ ላምቦርጊኒ እያሽከረከረ የነበረ ሲሆን አብረውት የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ግለሰቦች ደግሞ መርሴዲስ ጂ ዋገን ይዘው ነበር
"የለበስኩት የሚያምርብኝን እና ከማስተምራቸው ትውልዶች ጋር የሚያቀራርበኝን ነው። ስለዚህ የእጽ አዘዋዋሪዎች ሕይወት አይማርካቸውም" ብሏል።












