የሱቶን ግምት፡ ሊቨርፑል እና ዩናይትድ ያሸንፋሉ፣ ቼልሲ ይሸነፋል

ታትሟል

ባለፉት ስድስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሊቨርፑል እና ቶትንሃም አልተሸነፉም።

በሚቀጥለው እሁድ እርስ በእርስ ይገናኛሉ። ይህንን ያለመሸነፍ ጉዞ የትኛውን ቡድን ያስቀጥል ይሆን? ወይስ ነጥብ ተጋርተው ሁለቱም ያለመሸነፍ ጥንካሬያቸውን ያስጠብቃሉ?

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን “በእርግጠኝነት የቶትንሃሙ አዲሱ አሰልጣኝ ምትሃተኛነታቸውን ማስቀጠል ሊሳናቸው ይችላል” ብሏል። የሱቶን ሙሉ ግምቶች የሚከተሉት ናቸው።

ቅዳሜ የሚደረጉ ጨዋታዎች

አስቶን ቪላ ከ ብራይተን

Aston Villa VS Brighton

ይህ ጨዋታ ለመገመት በጣም ከባድ ነው። ምክንያቱም በኡናይ ኢምሬ የሚሰለጥኑት አስቶን ቪላዎች በእጅጉ መርህ አክባሪዎች ናቸው።

ቪላዎች በሜዳቸው ስለሚጫወቱ በብራይተን ላይ ጫና የመፍጠር ዕድሉ በእጃቸው ነው።

ነገር ግን ከብራይተን ጋር መጫወት ደግሞ ይህንን ለመተግበር አስቸጋሪ ነው።

በሁለቱም ቡድኖች ግቦች ይቆጠራሉ። ቪላም የተጠናከረ ቡድን በመሆኑ በጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት የተቻለውን ጥረት ያደረርጋል። በመሆኑም ጨዋታው በእኩል ውጤት ይጠናቀቃል።

ግምት፡ 2-2

Bournemouth VS Arsenal

ቦርንማውዝ ከ አርሰናል

የቦርንማውዝ ጉዞ አስተማማኝ አይደለም። አዲስ አሰልጣኝ ቢቀጥሩም ከበፊቱ አሰልጣኝ አንጻር የተለየ መሻሻል አይታይባቸውም።

አርሰናል ቡካዮ ሳካን ጨምሮ አሳሳቢ ጉዳቶች አሉበት። ቢሆንም ጨዋታውን እንደምንም ያሸንፋሉ።

ግምት፡ 0-1

Everton VS Luton

ኤቨርተን ከ ሉቶን

ኤቨርተኖች እየተሻሻሉ ነው። ሁለት ጨዋታዎችንም በተከታታይ አሸንፈዋል።

በሳምንቱ አጋማሽ አስቶን ቪላን ያሸነፉበት ጨዋታም ድንቅ ብቃታቸውን ያሳዩበት ነው። ያ የራስ መተማመን ለቀጣዩ ጨዋታ ትልቅ የራስ መተማመን ይፈጥርላቸዋል።

ሉቶን በካራባኦ ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ተሸንፏል። እንዲያም ሆኖ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀሉት ሉቶኖች ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም።

ጉዲሰን ፓርክ ላይ ይህንን ማሳካት የሚከብድ ሊሆን ይችላል።

በመሆኑም ኤቨርተን ይህንን ጨዋታ በቀላሉ ያሸንፋል።

ግምት: 2-0

Manchester Uited VS Crystal Palace

ማንችስተር ዩናይትድ ከ ክሪስታል ፓላስ

ከሦስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ባለፈው ሳምንት በርንሌይን ማሸነፋቸው ለኤሪክ ቴን ሃግ ትንፋሽ የሚሰጥ ነው።

በሳምንቱ አጋማሽ ክሪስታል ፓላስን ድል ማድረጋቸውም ሌላ ድል ነው። ሁለቱ ቡድኖች በድጋሚ ሲገናኙ ግን ጠንካራ አሰላለፍ ይዘው ነው የሚገናኙት።

ፓላሶች የሳምንቱ አጋማሽ ሽንፈታቸውን ለመበቀል ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም።

ቢሆንም ግን በሜዳው የሚጫወተው ማንችስተር ዩናይትድ በጠባብ የግብ ልዩነት ያሸንፋል።

ግምት: 2-1

Newcastle United VS Burnley

ኒውካስትል ከ በርንሌይ

ኒውካስትል አጀማመሩ በድል የታጀበ ባይሆንም አሁን እንደ አዲስ እያንሰራራ ነው።

ባለፈው ሳምንትም ሸፊልድ ላይ 8 ግቦችን አስቆጥሯል። ማንችስተር ሲቲን ባሸነፉበት የካራባኦ ዋንጫ ጨዋታም ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገዋል።

በጨዋታው የአሌክሳንደር አይዛክ ተቀይሮ መውጣት እና የሃርቬይ ባርነስ ጉዳት ለኒውካስትል አሳሳቢ ናቸው። ቢሆንም ግን እስካሁን ማሸነፍ የተሳነውን በርንሌይ በመርታት ጥሩ ውጤት ያስመዘግባሉ።

በርንሌይ አጨዋወታቸው ግሩም እና ወደፊት ተወርውሮ መጫወትን የሚመርጡ ቢሆኑም ግብ ማስቆጠር ላይ ግን ከባድ ፈተና ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላሉ። በመሆኑም ኒውካስትል በሜዳው በቀላሉ ይረታቸዋል።

ግምት: 4-0

WEST HAM VS SHEFFIELD UNITED

ዌስትሃም ከ ሸፊልድ ዩናይትድ

ሸፊልድ ዩናይትዶች ባለፈው ሳምንት በኒውካስትል የደረሰባቸውን ከባድ ሽንፈት ለማካካስ ከፍተኛ ትንቅንቅ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ጥረት ቢያደርጉም ወደ ለንደን ተጉዘው ነጥብ ይዘው ይመለሳሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።

ዴቪድ ሞይስ ቡድናቸውን እንዴት ማዘጋጀት እንዳለባቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ለሼፊልድ ቀላል አይሆኑላቸውም።

በተለይ ዌስትሃም ቀድሞ ካስቆጠረ ውጤቱን መቀልበስ ትልቅ ዳገት ይሆንባቸዋል።

ግምት: 2-0

Wolves VS Manchester City

ዎልቭስ ከ ማንችስተር ሲቲ

የማንችስተር ሲቲው አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ ለዚህኛው ጨዋታ ተቆጥቦ በኒውካስትል ዩናይትድ በተሸነፉበት የካራባኦ ጨዋታ አልተሰለፈም።

ሲቲ ጉዳቶች ያጋጠሙት ሲሆን ባለፈው ሳምንት ከኖቲንግሃም ጋር በነበረው ጨዋታ ቀይ ካርድ በመመልከቱ የመሃል ተጫዋቹ ሮድሪም አይሰለፍም።

ሲቲ ሃላንድን እና ጁሊያን አልቫሬዝን አጣምሮ ሲጫወት በጣም አስፈሪ ነው።

በመሆኑም ዎልቭስ የእነዚህን የፊት መስመር ተጫዋቾች ጥምረት ለማስቆም ከባድ ይሆንበታል።

ግምት: 0-3

Tottenham VS Liverpool

ቶትንሃም ከ ሊቨርፑል

የቶትንሃሙ አሰልጣኝ አንጌ ፖስቴኮግሉ ቶትንሃምን ማሰልጠን ከጀመሩ ጀምሮ አስገራሚ ውጤት እያስመዘገቡ ነው። ባለፈው አርሰናል ላይ ያሳዩትን ድንቅ ጨዋታም በሊቨርፑል ይደግሙታል ተብሎ ይጠበቃል።

ውጤቱን ለመገመት ከባድ ቢሆንም ብዙ ግብ የሚቆጠርበት ጨዋታ መሆኑ ግን አይቀሬ ነው። የቶትንሃሙ ሶን ጥሩ አቋም ላይ መሆኑ መልካም ቢሆንም የሊቨርፑሉ ዳርዊን ኑኔዝም በእጅጉ ተሻሽሏል።

ባለፉት ሳምንታት የተደረጉ ጨዋታዎችን ጠቅለል አድርገን ካየናቸው ድሉ ለሊቨርፑል የሚሆን ይመስላል።

ግምት: 2-3

Nottingjam Forest VS Brentford

እሁድ የሚደረጉ ጨዋታዎች

ኖቲንግሃም ከ ብሬንትፎርድ

ብሬንትፎርድ ከኤቨርተን ጋር በነበረው ጨዋታ ደካማ ጨዋታ አሳይቷል። ኖቲንግሃም ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን እስካሁን በሜዳው አልተሸነፈም። ቢሆንም ግን ያን ያክል ጠንካራ አይደሉም።

በመሆኑም ነጥብ ተጋርተው ሊወጡ ይችላሉ።

ግምት: 1-1

Fulham VS Chelsea

ፉልሃም ከ ቸልሲ

ቸልሲዎች የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ጨራሾች አይደሉም። በሳምንቱ አጋማሽ ብራይተንን ቢያሸንፉም አሳማኝ አይደለም።

በጨዋታው ብዙም ግብ የማይቆጠርበት ሲሆን ባለሜዳው ፉልሃም ድል ሊቀናው ይችላል።

ግምት: 1-0