ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የስኩዊድ ጌም ተዋናይ በወሲባዊ ትንኮሳ ክስ ተመሰረተባቸው
በኔትፍሊክስ ላይ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈው ተከታታዩ የስኩዊድ ጌም ተዋናይበኔትፍሊክስ ላይ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈው ተከታታዩ የስኩዊድ ጌም ተዋናይ ኦ ዮንግ ሱ በወሲባዊ ትንኮሳ ክስ እንደተመሰረተባቸው የደቡብ ኮሪያ የፍትህ ባለስልጣናት ገለጹ።
የ78 ዓመቱ ተዋናይ አንዲት ሴትን ጎንትለዋል፣ ያለ አግባብ ነክተዋል በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
ይህንንም የፈጸሙት በአውሮፓውያኑ 2017 ነበር ተብሏል።
ተዋናዩ ክሱን ማስተባበላቸውን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይ በኔትፍሊክስ በተሰራጨው ፊልም ላይ ባሳዩት ብቃት በምርጥ ደጋፊ ተዋናይ ዘርፍ የጎልደን ግሎብ ሽልማት በመቀዳጀት የመጀመሪያው የደቡብ ኮሪያዊ ተዋናይ ሆነዋል።
እንደ ዮንሃፕ የዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ ተበዳዩዋ ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ነው ለፖሊስ አቤቱታ ያቀረቡት። ነገር ግን በተዋናይ ኦ ዮንግ-ሱ ላይ ክስ ሳይመሰረት ጉዳዩ በሚያዝያ ወር ተዘግቷል።
አቃቤ ህግ "በተጎጂው ጥያቄ መሰረት" ምርመራውን እንደገና መጀመሩን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።
ተዋናዩ መታሰር ሳይጠበቅበት ተከሷል ሲልም አክሏል።
ክሱን ተከትሎ የሴኡል የባህል ሚኒስቴር ተዋናይ ኦ ዮንግ-ሱ የሚሳተፍበትን የመንግሥት ማስታወቂያ ለማቆም መወሰኑን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንን ጠቅሶ ዘግቧል።
ስኩዊድ ጌም የኔትፍሊክስ የምንጊዜም ተወዳጅ ተከታታይ ፊልም ነው።
ፊልሙ በእዳ የተዘፈቁ ሰዎች ላይ የሚያውጠነጥን ታሪክ ሲኖረው የልጆች ጨዋታዎችን በመጫወት ትልቅ የገንዘብ ሽልማት ለማግኘት የሚወዳደሩበት ነው።
ተዋናይ ኦ ዮንግ-ሱ በዕድሜ አንጋፋውን የጨዋታው ተሳታፊ ሆነው ተውነዋል።