ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቲክቶክ ባዘጋጀው የመጀመሪያው የአፍሪካውያን ቲክቶከሮች ውድድር ማን አሸነፈ?
በአፍሪካ አገራት ውስጥ ከፍተኛ ተጠቃሚዎችን እያፈራ ያለው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ቲክቶክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለየ የቪዲዮ ይዘት ያቀረቡ አፍሪካውያንን ሸለመ።
በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ላይ በተካሄደ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት ከቀረቡ ቲክቶከሮች መካከል ነው ምርጫ የተደረገው።
ቲክቶክ “ባለፈው ዓመት ከፍ ያለ ተሰጥኦን እና ፈጠራን በማኅበራዊ መድረኩ ላይ ያቀረቡ” በሚል ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት በዕጩነት ቀርበዋል።
ቲክቶከሮች በመባል የሚታወቁት የማኅበራዊ ሚዲያው ተሳታፊዎች የተለያዩ ይዘቶች ያላቸውን አጫጭር ቪዲዮዎችን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ በውድድሩ ላይ የቀረቡት አብዛኞቹ የአፍሪካ ዕጩዎች የምግብ ማብሰል፣ የውበት አጠባበቅ እና የዳንስ ችሎታን ያቀረቡ ናቸው።
በዚህ በአፍሪካ የቲክቶች ተሳታፊዎች የመጀመሪያው ሽልማት የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ ተሳታፊዎችን ማበራታት አላማው እንደሆነ የቲክቶክ የሰሃራ በታች አፍሪካ የይዘት ኃላፊ ቦኒስዋ ሲድዋባ ተናግረዋል።
ጨምረውም “ቲክቶክ ለይዘት አቅራቢዎቹ የሚገባቸውን ዕውቅና በመስጠት አፍሪካዊ የሆኑ ታሪኮችን እንዲያቀርቡና ሁሌም ደስ የሚያሰኝ ነገርን ለሌሎች እንዲያጋሩ ማበረታት ነው” ብለዋል።
ውድድሩ የተካሄደው አፍሪካን በአራት አካባቢዎች በመክፈል ሲሆን በዚህም የተለያዩ ቲክቶከሮች ሥራዎች በምሥራቅ አፍሪካ፣ በምዕራብ አፍሪካ፣ ከሰሃራ በታች አፍሪካ እና በደቡብ አፍሪካ ክልሎች ተከፋፍለው ቀርበዋል።
በውድድሩ ላይ በዕጩነት ከቀረቡት እና አሸናፊ ከሆኑት መካከል ናይጄሪያውያን፣ ኬንያውያን እና ደቡብ አፍሪካውያን ሰፊውን ቦታ ተቆጣጥረውታል።
በዚህም መሠረት ከምሥራቅ አፍሪካ እና ከሰሃራ በታች አፍሪካ ባለው ምድብ ኬንያውያኑ ናታሻ ግዋል እና ዴኒስ ኦምባቺ ሲያሸንፉ፣ ከምዕራብ አፍሪካ ናይጄሪያዊው ኢፌኦማ ኢፊኦክዋ፣ ከደቡብ አፍሪካ ደግሞ ደቡብ አፍሪካዊቷ ሜሊሳ አሸናፊ ለመሆን ችለዋል።
ሁለተኛ ደረጃን የያዙት ደግሞ ከምሥራቅ አፍሪካ ኬንያዊ፣ ከሰሃራ በታች ናይጄሪያዊ፣ ከምዕራብ አፍሪካ ናይጄሪያዊ እና ከደቡብ አፍሪካ ደቡብ አፍሪካዊ ሆነዋል።
ተወዳዳሪዎቹ በተለያየ የሙያ ዘርፍ ያላቸውን ክህሎት፣ የተለያዩ ፈጠራዎችን እና ባህልን በሠሯቸው አጫጭር የቲክቶክ ቪዲዮዎች በማሳየት ነው ለመመረጥ የበቁት።
በአፍሪካ ውስጥ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ሲሆን፣ በተለይ በኬንያ፣ በግብፅ እና በናይጄሪያ ውስጥ የተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመሩን መረጃዎች ያሳያሉ።
ቲክቶክ በኢትዮጵያ ውስጥም የተለያዩ አይነት የቪዲዮ ይዘቶችን የሚፈጥሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው ቲክቶከሮች እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ተጠቃሚዎች አሉት።