በካቡል የመስጊድ ጥቃት በርካቶች ሞቱ

በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል በደረሰ አንድ የመስጊድ ውስጥ የቦምብ ጥቃት በርካታ ሰዎች ሞቱ።
በምሽት ሰዓት ይደረግ በነበረ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ነው ቦምቡ የፈነዳው።
እስከአሁን በጥቃቱ ሦስት ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ቆስለዋል።
የታሊባን ፖሊስ ቃል አቀባይ ካሊድ ዛድራን በሰሜን ምዕራብ ካቡል ሌላ ፍንዳታ እንደተሰማ ለአገሬው ሚዲያ ተናግረዋል።
ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በዚህ የትናንቱ ፍንዳታ የሲዲቂ መስጊድ ኢማምን ጨምሮ የበርካቶች ሕይወት አልፏል።
እስከአሁን ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ የታወቀ ነገር የለም።
አንድ የታሊባን አስተዳደርን በመደገፍ የሚታወቁ መንፈሳዊ መሪ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በሌላ ፍንዳታ መገደላቸው የሚታወስ ነው።
ለዚያ ጥቃት አይ ኤስ ኃላፊነቱን ወስዶ ነበር።
አንድ በካቡል ቅርንጫፍ ቢሮ ያለው የጣሊያን የረድኤት ድርጅት በትናንቱ ጥቃት ሦስት ሰዎች ስለመሞታቸውና 27 ሰዎች ክፉኛ ስለመቁሰላቸው ማረጋገጫ ሰጥቷል።
ከቆሰሉት መካከል የሰባት ዓመት አዳጊን ጨምሮ በርካታ ሕጻናት ይገኙበታል።
አንድ የታሊባን የደኅንነት ባለሥልጣን ለሮይተርስ እንደተናገሩት ደግሞ በድምሩ 35 ሰዎች ተገድለዋል፣ በርካቶች ቆስለዋል። እንደ እርሳቸው ከሆነ ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ ይችላል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይኤስ በአፍጋኒስታን የታሊባን አገዛዝን የሚቃወም ሁነኛ ተገዳዳሪ ሆኖ እየወጣ ነው።
ይህ ቡድን በተለይ በሺአ ሙስሊሞች ላይ ተከታታይ ጥቃት በማድረስ ይታወቃል።
ታሊባኖች የአሜሪንን ጦር ከካቡል መልቀቅን ተከትሎ አገሪቱን በእጃቸው ካስገቡ በቅርብ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል።












