ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"በጭንቀት ልንፈነዳ ደርሰናል" – በፌደራል እና በትግራይ የ12ተኛ ክፍል ፈተና ውዝግብ ግራ የተጋቡት ተማሪዎች
የትግራይ ክልል የ12ተኛ ክፍል የወረቀት ተፈታኞችን የጊዜ ሰሌዳ በተመለከተ በክልሉ ትምህርት ቢሮ እንዲሁም በፌደራሉ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ግራ መጋባት ውስጥ እንደከተታቸው የክልሉ ተማሪዎች ተናገሩ።
ከሰኔ 23/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በስድስት ዙሮች በበይነ መረብ እና በወረቀት መሰጠት በጀመረው በዘንድሮው የ12ተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከ563 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚፈተኑ ተገልጿል።
በመጨረሻዎቹ ዙሮች የሚካሄደው የወረቀት ፈተና ከሐምሌ 1 እስከ 17 እንደሚካሄድ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቆ ነበር።
ይሁን እንጂ በትግራይ ክልል የሚካሄደው የወረቀት ምዘና ቀኑ ተራዝሞ ከሐምሌ 22 ጀምሮ ለሦስት ቀናት እንዲካሄድ መወሰኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እሸቱ ከበደ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሚመራው የክልሉ አስተዳደር ሥር የሚገኘው የትምህርት ቢሮ የጊዜ ሰሌዳ ለውጡን አልተቀበለውም። ትምህርት ቢሮው የቀን ለውጡን "ፖለቲካዊ ውሳኔ" እና "በትግራይ ሕዝብ ላይ በተለያየ መንገድ እየተፈጸመ የመጣው እና እየቀጠለ ያለው ጥቃት አካል" ሲል ገልጾታል።
ትምህርት ሚኒስቴር አገር አቀፉን ፈተና በተመለከተ "እርስ በራሳቸው የሚጣረሱ፣ ግልፅነት የጎደላቸው፣ በየጊዜው የሚቀያየሩ" ውሳኔዎች አሳልፏል በማለትም ሰኞ ሐምሌ 6 ቀን ለፌደራል ትምህርት ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ ወቅሷል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ በክልሉ ለሚገኙ ተማሪዎች የራሱን ፈተና አውጥቶ እንደሚሰጥም አስታውቋል።
አገር አቀፍ ፈተናዎችን የማስተደዳር ሥልጣን ያለውን መሥሪያ ቤት የሚመሩት ዶ/ር እሸቱ በበኩላቸው ከትግራይ ውጪ "በሌሎች ክልሎችም ላይ በተለያየ ምክንያት" በእነዚህ ቀናት ፈተናውን የሚወስዱ ተማሪዎች እንዳሉ ይናገራሉ።
የፌደራሉ ተቋም የጊዜ ሰሌዳ የሚያወጣው ፈተናውን "ለመስጠት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን" ከግምት ውስጥ አስገብቶ መሆኑን የሚገናሩት ዶ/ር እሸቱ፤ የትግራይ ክልል ፈተና ቀን ያስነሳው ጥያቄ እንደማይዋጥላቸው ገልጸዋል።
"ለምን ዛሬ ላይ እንደተነሳ ባይገባኝም ትግራይ ክልል ላይ ሁለት ጊዜ ከዚህ በፊት በተለየ ፕሮግራም ሰጥተናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"አሁን ወቅታዊ ካለው አንዳንድ የፖለቲካ ጉዳዮች ጋር አገናኝቶ የፖለቲካ ገበያ ለመገበያየት ማድረጉ ተገቢ አይደለም" በማለትም ይወቅሳሉ።
ፌደራል መንግሥት ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ እና የትግራይ ትምህርት ቢሮ ውሳኔ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት የክልሉ ተማሪዎች ጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን በሰመማ ከተማ የምትማረው መርሐዊት ግደይ፣ በዚህ ብሔራዊ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማምጣት ጠንክራ ስታጠና ቆይታለች። ለሐምሌ 1 ቀን ሊሰጥ የነበረው ፈተና ቀን ሲቀየር እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ የራሱን ፈተና እንደሚያዘጋጅ ሲያስታውቅ ግራ እንደተጋባች ትናገራለች።
"በጭንቀት ልንፈነዳ ደርሰናል። ግራ መጋባት ውስጥ ነው ያለነው። ሐምሌ 22 ትፈተናላችሁ እንባላለን፤ ወደ ወረዳ መምህራን ስንደውል ደግሞ 'ገና ቀኑ አልተወሰነልንም' ይሉናል። ሜዳ ላይ ቀርተን እየጠበቅን ነው" ትላለች።
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ፤ "በተወሰኑ የመሠረተ ልማት ጉድለት ባለባቸው አካባቢዎች በወረቀት በተለያዩ አራት ዙሮች ማለትም ለተፈጥሮ ሳይንስ፣ ለማኅበራዊ ሳይንስ እንዲሁም በቀድሞ ሥርዓተ ትምህርት ለተማሩ እና የትግራይ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች በስድስቱ ዙር ላልተፈተኑ ተፈታኞች ከበይነ መረቡ ፈተና ጎን ለጎን በወረቀት ፈተና እየሰጠ ይገኛል" ብሏል።
ከሐምሌ 22 እስከ 24/ 2018 ዓ. ም. የሚሰጠው ፈተና በመቀለ ዩኒቨርሲቲ እና በአክሱም ዩኒቨርሲቲ እንደሚካሄድም ይጠቅሳል።
በሰሜናዊ ምዕራብ ትግራይ አዲ ዳእሮ የፈተናና ምዘና ሒደት አስተባባሪ እና መምህር የሆኑት አቶ ተስፋይ ገብረእግዚአብሔር እንደሚናገሩት የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና ሐምሌ 1 እና የማኅበራዊ ሳይንስ ሐምሌ 6 እንደሚሰጥ ከአንድ ወር በፊት ተገልጾ ነበር።
"ነገር ግን በ28 ፈተናው ተራዝሟል ሲባል ወላጆች እና ተማሪዎች በጣም ነው የተጨነቁት" ብለዋል።
"ፕሮግራም ወጥቶ የደከሙበት እና ውጤት የሚያይዩበትን [ፈተና] እየጠበቁ ስለነበር ተራዝሟል ሲባል በጣም ነው የተደናገጡት።"
ለምን የትግራይ ብቻ እንደዚህ ሆነ? የሚለው ጥያቄ ወላጆች እና ልጆችን "መጨነቅ እና ተስፋ መቁረጥ" እንደከተታቸውን ገልጸዋል።
የትግራይ የትምህርት ቢሮ እና የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አንድ ላይ ሆነው የተራዘመበትን ምክንያት አለመግለጻቸው ተማሪዎቹን "እንደረበሻቸው" አቶ ተስፋይ አክለዋል።
"ተማሪዎች እንኳን ተረጋግቶ ፈተና መግባት ጭንቅ ላይ ነው ያሉት። እኛም መልስ የለንም" ብለዋል።
ለትግራይ ክልል "የተለየ ፈተና የሚዘጋጅ ከሆነ ተቀባይነት የለውም" ያሉት አቶ ተስፋይ "ተማሪዎች ለ12 ዓመት የለፉበትን ሥራ ውጤት ለማየት ተቸግረዋል. . . የፖለቲካ ችግር ካለም ተማሪዎቹ የኢትዮጵያ፣ የትግራይ ተረካቢ ዜጎች ናቸውና ችግራ ይፈታ" በማለትም አሳስበዋል።
የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና የሚፈተነው ክብሮም ፀጋይ እንደሚለው የፈተና ጊዜ ሰሌዳን በተመለከተ የተፈጠረው ውዝግብ "ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና አሳድሮበታል"።
ለፈተናው በየቀኑ ሲዘጋጅ እንደነበር ጠቅሶ አሁን ላይ ግን "በሕይወቴ በጣም ተስፋ ቆርጫለሁ" ሲል ያለበትን ጭንቀት ገልጿል።
ለአገራዊ ፈተናው ሲያጠና እንደቆየ ገልጾ አሁን የተፈጠረው ውዝግብ "አእምሮዬ ላይ ጫና ፈጥሯል" ብሏል።
ፈተናው የሚሰጥበት ትክክለኛ ቁርጥ ቀን እንዲነገረው እንደሚፈልግም አክሏል።
ሌላዋ ተማሪ ማኅደር ልዑል "ለምንድን ነው ሐምሌ 22 የሆነው? እኛ ኢትዮጵያዊ መሆናችንን በምንድን ነው የምናውቀው?" ስትል ትጠይቃለች።
ለፈተናው ስትዘጋጅ እንደቆየች ጠቅሳ "12ኛ ክፍል መማሬን ጠላሁት። ጓደኞቼ ተስፋ ቆርጠው በሊቢያ እንሰደድ እያሉ ነው" ብላለች።
ሐምሌ 22 ፈተናው ይሰጣል ከተባለ በኋላ መጀመሪያ ላይ እንደነበረው ያህል ለፈተና የመዘጋጀት ተነሳሽነት እንደሌለ ጠቅሳለች።
"ፖለቲካ ለምን በ12ኛ ክፍል ፈተና ውስጥ ገባ?" ስትልም ማኅደር ትጠይቃለች።
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ማክሰኞ ሐምሌ 7/2018 ዓ.ም. ባወጣው ማስታወቂያ በትግራይ ክልል እና በሌሎችም አካባቢዎች ፈተናው የሚሰጥበትን ጊዜ ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሠረት በትግራይ ክልል ውስጥ ፈተናው ከሐምሌ 22 አስከ 24 ድረስ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ አስታውቋል።