የአሜሪካ የበሽታዎች መከላከያ ኃላፊ፣ ሲዲሲ ዳይሬክተር ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ዳይሬክተር ዋይት ሐውስ ከሥልጣን መባረራቸውን ካስታወቀ በኋላ ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገለፁ።

በኃላፊነቱ ላይ ለአንድ ወር ብቻ የቆዩት ሱዛን ሞናሬዝ "ሳይንሳዊ ላልሆኑ እና ግድየለሽነት ለተሞላባቸው መመሪያዎች ይሁንታን አልሰጥም" ማለታቸውን እንዲሁም የጤና ጥበቃ ፀሐፊ ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር "የኅብረተሰብ ጤናን እንደ መሳርያ ተጠቅመዋል" በማለት መክሰሳቸውን ጠበቆቻቸው ተናግረዋል።

ጠበቃቸው የዶ/ር ሞናሬዝ መባረር ሕጋዊ እንዳልሆነ እና ዋይት ሐውስ ሳይሆን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ብቻ ከሥልጣን ሊያባርሯቸው እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ከሥልጣን የተባረሩበት ምክንያት "ከፕሬዚዳንቱ አጀንዳዎች ጋር ባለመስማማት" መሆኑን ዋይት ሐውስ በመግለጫው ላይ ገልጿል።

ዶ/ር ሞናሬዝ በምትካቸው ጂም ኦኔል እንደሚተኩ የቢቢሲው የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዘግቧል።

አዲሱ ተሿሚ የጤና ኤጀንሲ ተጠባባቂ ዳይሬክተር በመሆን ያገለግላሉ።

ኦኔል የቀድሞ የቴክኖሎጂ ባለሀብት እና በአሁኑ ጊዜ በኬኔዲ ስር የሄዝ እና ሰብዓዊ አገልግሎት ምክትል ፀሐፊ ናቸው።

ዶ/ር ሱዛን ሞናሬዝ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው በጤና ሚኒስቴሩ በኩል ይፋ ከሆነ በኋላ ወዲያውኑ ሦስት የሲዲሲ ከፍተኛ መሪዎች ሥራቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል።

ከእነዚህም መካከል ክትባትን በሚመለከት የጨመረው ሐሰተኛ መረጃዎች ሥርጭት አደገኛነቱን በደብዳቤ ያሳሰቡት የሜዲካል ኃላፊ ዴብራ ሆሪ ይገኙበታል።

ኃላፊዋ የተቋሙን በጀት ለመቀነስ የተያዘውን እቅድም የተቃወሙ ናቸው።

ዳንኤል ጀሪንገን እና ዲሜትሪ ዳስካልስኪ የተባሉ ከፍተኛ ኃላፊዎችም በጤናው ዘርፍ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመጥቀስ ሥራቸውን ለቀዋል።

የፌደራል መንግሥቱ የረጅም ጊዜ ተመራማሪ የነበሩት ዶ/ር ሱዛን፣ ሲዲሲን ለመምራት በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእጩነት ከቀረቡ በኋላ ባለፈው ሐምሌ ነበር ሹመታቸው የፀደቀው።

ዶ/ር ሞናሬዝ ለእጩነት የቀረቡት የትራምፕ የመጀመሪያ ምርጫ የቀድሞው የሪፐብሊካን የምክር ቤት አባል ዴቭ ዌልደን ክትባት ላይ እና ኦቲዝምን በሚመለከት ያላቸው ዕይታ ውዝግብ ካስነሳ በኋላ ነው።

ረቡዕ ዕለት የዶ/ር ሞናሬዝ ጠበቆች "ፖለቲካዊ አጀንዳን ከማገልገል ይልቅ ሕዝቡን መጠበቅ መርጣለች" ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

የዋይት ሐውስ መግለጫ የሥልጣን ዘመናቸው መቋረጡን ያስታወቀ ሲሆን "የጠበቃዋ መግለጫ በግልፅ እንደሚያሳየው ሱዛን ሞናሬዝ ከፕሬዚዳንቱ አጀንዳ ጋር አልተጣጣመችም" ብሏል።

ሐሙስ ዕለት ኬኔዲ በፎክስ ኒውስ ላይ የሲዲሲ አመራር "የትራምፕን አጀንዳ ማስፈፀም አለበት" ብለዋል።

አክለውም ሲዲሲ "ችግር ውስጥ ነው፣ መስተካከል አለበት" ብለዋል።

ኒውዮርክ ታይምስ የሲዲሲ ዳይሬክተሯ ከኬኔዲ ጋር በክትባት ፖሊሲ የተነሳ አለመግባባት ውስጥ እንደነበሩ ዘግቧል።

ዋይት ሐውስ ተተኪያቸውን በቅርቡ እንደሚሾም ተናግሯል።

የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ሐሙስ ዕለት "ሰዎች ይህችን አገር እንደገና ጤናማ ለማድረግ ከፕሬዚዳንቱ እና ከፀሐፊያቸው ራዕይ ጋር ካልተጣጣሙ፣ በደስታ በሩን እናሳያቸዋለን" ብለዋል።

የዓለማችን ግንባር ቀደም የጤና ተቋም ሲዲሲ ዳይሬክተር ስንብት የተሰማው የጤና ባለሙያዎች በክትባት በማያምኑት ኬኔዲ መሪነት የተቋሙን በሽታ የመከላከል አካሄድ በሚመለከት ስጋታቸውን እየገለፁ ባለበት ወቅት ነው።

ረቡዕ ዕለት የአገሪቱ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር አዲስ የኮቪድ ክትባትን ማን መውሰድ እንዳለበት በመገደብ አፅድቋል።

ክትባቱን ሁሉም አዋቂ ሰዎች ማግኘት የሚችሉ ቢሆንም ከበሽታው ጋር የተያያዙ የጤና እክሎች የሌለባቸው ወጣቶች እና ሕፃናትን ግን ያገለለ ነው።

ዶ/ር ሞናሬዝ በ50 ዓመታት ውስጥ የሜዲካል ዲግሪ የሌላቸው የመጀመሪያዋ የሲዲሲ ኃላፊ ናቸው።

የትምሕርት ልምዳቸው የተላላፊ በሽታዎች ምርምር ላይ ነው።

በወሩ መጀመሪያ የቀድሞ እና የአሁን የተቋሙ ሠራተኞች ለሕዝብ ዕይታ በዋለ ደብዳቤ የጤና ሚኒስትሩ ኬነዲ በፀረ ክትባት ንግግራቸው የጤና ባለሙያዎች ላይ ጥቃት እያነሳሱ ነው ሲሉ ከሰዋል።

የዶ/ር ሞናሬዝ ከሥራ መሰናበት የመጣው ተቋሙ 600 ሠራተኞችን ማባረሩን የሠራተኛ ማኅበር ባሳወቀ በሳምንት ውስጥ ነው።