ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የብረት እና የአሉሚኒየም ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጣሉ

ብረታ ብረት ሲመረት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የብረት እና የአሉሚኒየም ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል።

ይህን ታሪፍ ተከትሎ ወደ አሜሪካ ብረታ ብረት የሚያስገቡ ነጋዴዎች ላይ ጫና የሚበረታ ሲሆን፣ የካናዳ ፖለቲከኞች የትራምፕ ውሳኔ ሁኔታዎችን ያወሳስባል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ካናዳ ወደ አሜሪካ ብረታ ብረት ከሚልኩ ሀገራት መካከል ቁንጮዋ ናት።

ብረታ ብረት የሚያስገቡ የአሜሪካ ድርጅቶች የትራምፕ ውሳኔ እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል። ነገር ግን ትራምፕ ይህ ታሪፍ የሀገር ውስጥ ምርትን ከፍ ያደርጋል ብለው ያስባሉ።

ትራምፕ ያስተላለፉት የታሪፍ ጫና ከአውሮፓውያኑ መጋቢት 4/2025 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።

ፕሬዝደንቱ "ይህ ትልቅ ነገር ነው። አሜሪካን ሀብታም የምናደርግበት ጅማሬው አሁን ነው" ብለዋል።

"ሀገራችን የሚያስፈልጋት አሜሪካ ውስጥ የተመረተ ብረት እና አሉሚኒየም እንጂ ከውጭ የሚመጣ አይደለም" ሲሉ አክለዋል።

ፕሬዝደንቱ በምርቶቹ ላይ የጫኑት ታሪፍ ሸማቹ ማኅበረሰብ ላይ የዋጋ መናር ያስከትል ይሆን ተብለው የተጠየቁት ትራምፕ "ቀስ በቀስ ርካሽ መሆኑ አይቀርም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ በዓለማችን ቁጥር አንድ የብረታ ብረት አስገቢ ስትሆን ካናዳ፣ ብራዚል እና ሜክሲኮ ደግሞ ሦስቱ ዋነኛ አቅራቢዎች ናቸው።

ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ብቻ ካናዳ ወደ አሜሪካ ከገቡ ብረታ ብረቶች መካከል 50 በመቶውን አቅርባለች። ታሪፉ ተግባራዊ መደረግ ሲጀምር ጫናው ካናዳ ላይ እንደሚበረታ ይጠበቃል።

ሰኞ ምሽት አስተያየት የሰጡት የካናዳ የኢኖቬሽን ሚነስትር ፍራንሷ-ፊሊፕ ሻማፓኝ የአሜሪካው ፕሬዝደንት የጣሉት ታሪፍ "በፍፁም ምክንያታዊ አይደለም" ብለዋል።

የካናዳ የብረታ ብረት አምራቾች በወኪላቸው በኩል የካናዳ መንግሥት "በአፋጣኝ" የአፀፋ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የገዢው ሊበራል ፓርቲ አባል እና የሕዝብ እንደራሴው ኮዲ ብሏ ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለመቀነስ መላ እየዘየደች እንደሆነ ተናግረዋል።

ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የብረት ምርቶች ላይ የ25 በመቶ፤ የአሉሚኒየም ምርቶች ላይ ደግሞ የ15 በመቶ ታሪፍ ከጣሉ በኋላ ከአውስትራሊያ፣ ከካናዳ እና ከሜክሲኮ ጋር ስምምነት ደርሰው ውሳኔያቸውን መሰረዛቸው ይታወሳል።

ተንታኞች ዶናልድ ትራምፕ ታሪፍ የሚጥሉት ከሀገራት ጋር ከስምምነት ለመድረስ እንደመሟገቻ መንገድ እንጂ አይቀጥሉበትም የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።

ታሪፍ ማለት የሀገር ውስጥ ግብር ሲሆን፣ ምርቶች ከውጭ ሀገራት ሲመጡ የሚጣል ነው።

የዓለም ሀገራት መሪዎች የትራምፕ የታሪፍ ውሳኔ ያሳሰባቸው ይመስላል። ምክንያቱም የትራምፕ ታሪፍ አምራቾች ለዓለማችን ትልቋ ኢኮኖሚ ምርታቸውን ለመሸጥ አዳጋች አድርጎባቸዋል።