እስራኤል ባደረሰችው የአየር ጥቃት በትምህርት ቤት የተጠለሉ ቢያንስ 54 ሰዎች ተገደሉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው የአየር ጥቃት በትምህርት ቤት ሕንጻ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ቢያንስ 54 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የሆስፒታል ዳይሬክተሮች ለቢቢሲ ገለጹ።

በጋዛ የሚገኘው ፋሀም አል-ጃርጋዊ ትምህርት ቤት በመቶዎች የሚቆጠሩ ከቤት ላህያ የተፈናቀሉ ሰዎች ተጠልለውበታል። እስራኤል በአካባቢው ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸመች ነው።

ከተገደሉት 54 ሰዎች መካከል ትምህርት ቤቱ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ቢያንስ 35 ሰዎች እንደሚገኙበትና የተቀሩት በአካባቢው ተጠልለው እንደነበር ተገልጿል።

ሐማስ የሚመራው የጋዛ መከላከያ እንዳለው ሁለት መጠለያ የነበሩ ክፍሎች በእሳት ከጋዩ በኋላ የሕጻናትን ጨምሮ ብዙ አስክሬኖች በቦታው ታይተዋል። ሰውነታቸው እንደተቃጠለም ተገልጿል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር "የሐማስና ኢስላሚክ ጂሀድ መቆጣጠሪያ" ዒላማ ማድረጉን አስታውቋል።

አካባቢው "አሸባሪው ጥቃት ለማቀነባበር የሚጠቀምበት ነው። የጋዛን ሕዝብ እንደ ከለላ እየተጠቀመ ነው" ሲልም ገልጿል።

ሕጻናትን ጨምሮ ብዙ ሰዎች በእሳት ተቃጥለው የሚያሳዩ አሰቃቂ ቪድዮዎች ወጥተዋል። በሕይወት የተረፉ ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታያል።

በሰሜን ጋዛ የአምቡላንስ አገልግሎት ሰጪ ኃላፊ ፋሪስ አፋና እንዳለው በቦታው ሲደርስ መማሪያ ክፍሎች ጋይተዋል።

"የተኙ ሕጻናትና ሴቶች ነበሩ። እየጮሁ ነበር። እሳቱ ስለከበባቸው ልናድናቸው አልቻልንም። በጣም አሰቃቂ ስለሆነ ያየሁትን መናገር አልችልም" ይላል።

የሐማስ ፖሊስ ዋና መርማሪ ሞሐመድ አል-ካሺህ ከባለቤቱና ልጆቹ ጋር ተገድሏል።

የአል አህሊ ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶ/ር ፋደል ኢልናይም እንዳሉት በጃባሊያ በደረሰ ሌላ ጥቃት 19 ሰዎች ተገድለዋል።

በቦታው ምን ዒላማ እንዳደረገ የእስራኤል መከላከያ አልገለጸም።

እስራኤል ያደረሰቻቸው ሁለት የአየር ድብደባዎች በሰሜናዊ ጋዛ በስፋት የቀጠለችው ጥቃት አካል ናቸው፥

በ48 ሰዓታት ውስጥ 200 ዒላማ መምታቱን የእስራኤል መከላከያ አስታውቋል። እነዚህንም "የአሸባሪዎች መቀመጫ" ብሏቸዋል።

ከፍተኛ የሐማስ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ በቅርቡ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ስቲብ ዊትኮፍ ባቀረቡት የተኩስ አቁም ስምምነት ተስማምተዋል።

ዊትኮፍ ግን ካቀረቡት የተኩስ አቁም ሐሳብ የተለየ መቅረቡን ገልጸው "ተቀባይነት የለውም" ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

በእስራኤል በኩል ይህ ዕቅድ ተቀባይነት እንደማይኖረው ጭምጭምታ ተሰምቷል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ጥረቶች ቢቀጥሉም፣ ባለፈው ሳምንት ፍልስጤማዊ ሐኪም በሚኖርበት ቤት በደረሰ ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባል ከሆኑ 10 ልጆች ዘጠኙ ተገድለዋል።

ዘጠኙ ልጆች- ያህያ፣ ራካን፣ ሳስላን፣ ገብራን፣ ኢቭ፣ ሪቫል፣ ሳይደን፣ ሉቅማን እና ሲድራ ከወራት ዕድሜ እስከ 12 ዓመት ይደርሱ ነበር። የተረፈው ወንድማቸው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል ገብቷል።

በካሀን ዩኑስ በደረሰ ጥቃት የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ሠራተኞች መገደላቸው ተገልጿል።

በጋዛ በግል ተቋማት በኩል እርዳታ ለማድረስ አሜሪካ በእስራኤል መንግሥት ይሁንታ ያቋቋመችው ተቋም ለመሥራት ፈቃድ አግኝቷል።

የጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ዋና ኃላፊ ጄክ ውድ ግን ይህ ተቋም ገለልተኛ ስላልሆነ "የሰብአዊ እርዳታ መስፈርትን አያሟላም" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ሌሎችም የተራድኦ ተቋማት ድርጅቱ በመድልዎ ስለሚሠራ አብረውት እንደማይሠሩ አስታውቀዋል።

እስራኤል ለ11 ሳምንታት ጋዛን ሙሉ ከበባ ውስጥ አስገብታለች። መድኃኒትና ምግብ ወደ ጋዛ ማስገባት አልተቻለም።

ወደ ጋዛ ባለፈው ሳምንት 107 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ መፈቀዱን እስራኤል ብትገልጽም፣ ተመድ እንዳለው በየቀኑ ከ500 እስከ 600 መኪና እርዳታ መግባት አለበት።

ያለፈው እሑድ 20 አገራትና ተቋማት በማድሪድ ተናኝተው የገዛን ጦርነት ለማስቆም ተወያይተዋል። የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆዜ ማኑኤል አልባሬስ እስራኤል ጥቃት ካላቆመች የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል።

እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት እስካሁን ቢያንስ 53,939 ሰዎች መገደላቸውንና ከእነዚህም መካከል 16,500 ሕጻናት እንደሆኑ ተገልጿል።