በዩክሬን ጦርነት የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ማዕቀቦችን ጥሰዋል- አሜሪካ

በሩሲያ ድሮን የተመታው የኪዬቭ ህንጻ ፍርስራሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ኢራን ለሩሲያ የምታቀርባቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጣለውን ማዕቀብ ይጥሳል ሲሉ ምዕራባውያን አጋሮች ከተናገሩት ጋር እንደምትስማማ አስታወቀች።

ኪዬቭ ሰኞ ዕለት "ካሚካዜ" በሚባሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተመታለች። ጥቃቱ በሩሲያ የተሰነዘረ ቢሆንም በኢራን የተሠራ ነው ተብሎ ይታመናል።

አሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 2231ን ጥሰዋል በሚል ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ባደረጉት ግምገማ እንደምትስማማ የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከኢራን የኒውክሌር ስምምነት ጋር የተገናኘው ይህ ውሳኔ ኢራን አንዳንድ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን አሳልፋ እንዳትሰጥ ይከለክላል።

ዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖቹን የኢራኖቹ ሻሄድ-136 እንደሆኑ ለመለየት ችላለች። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ራስን የማጥፋት ተልዕኮ ከፈጸመ ጃፓናዊ አብራሪ ነው ስሙን አግኝቶ ካሚካዜ ድሮን የተባለው።  

“እነዚህ ከኢራን ወደ ሩሲያ የተዘዋወሩ እና ሩሲያ ደግሞ ዩክሬን ላይ የተጠቀማቸው ድሮኖች በ2231 እገዳ ተጥሎባቸው ከነበሩት መሣሪያዎች መካከል እንደሆኑ እምነታችን ነው" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሆኑት ቬዳንት ፓቴል ተናግረዋል።

ኢራን ለሩሲያ ድሮን ማቅረቧን አስተባብላለች። ዩናይትድ ስቴትስ ግን "ሩሲያ ከኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መቀበሏን አጋልጣ፣ ይህም ሩሲያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢራን ድሮኖችን ለማስገባት ያቀደችው አካል ነው" ብለዋል ፓቴል።

ሩሲያ ድሮኖቹን በዩክሬን መጠቀሟን የሚያሳዩ “በርካታ ማስረጃዎች” እንዳሉም ተናግሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሰኞው ጥቃት በዩክሬን ወሳኝ የሚባሉ የመሠረተ ልማት አውታሮች ኪዬቭ፣ ዲኒፕሮ እና ሱሚ ግዛቶች ውስጥ መመታታቸውንና በበርካታ ከተሞች መብራት መቀወረጡን ኪዬቭ ገልጿል።

በኪዬቭ እና በሱሚ የተገደሉትን አራት አራት ሰዎች ጨምሮ ቢያንስ ስምንት ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። አሜሪካ “ለተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች [ሩሲያን] ተጠያቂ አደርጋለሁ” ብላለች::

ፓቴል አክለውም በራሺያ እና በኢራን መካከል እየተጠናከረ የመጣውን ትብብር መላው ዓለም እንደ ስጋት ሊመለከተው ይገባል ብለዋል። ሩሲያ እና ኢራን በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ለፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ቁልፍ ወታደራዊ ድጋፎችን አድርገዋል።

"ከኢራን ጋር ከድሮን ወይንም ባለስቲክ ሚሳኤሎች ጋር ተያይዞ ግንኙነት ያላቸውው አካላት ከቴህራን ወደ ሩሲያ በሚፈሰው የጦር መሣሪያ ውስጥ ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል። ስለዚህ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። አሜሪካ ማዕቀብ ከመጣል ወደኋላ አትልም" ሲሉ ፓቴል አስጠንቅቀዋል።

የሰኞው ጥቃት የደረሰው ሩሲያ በደርዘን የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችን በኪዬቭ እና በሌሎች የዩክሬን ከተሞች የሚገኙ የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ከተተኮሰች ከሳምንት በኋላ ነው። የምዕራባውያን ተንታኞች እንደሚሉት ሩሲያ የረዥም ርቀት ጥቃቶችን እንድትቀጥል ኢራን እየረዳቻት ነው ብለው ያምናሉ።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል እንዳሉት የአውሮፓ ህብረት በኢራን ድሮኖች ላይ “ማስረጃ እየሰበሰበ ነው።” ማዕቀቦችን ሊያጠናክሩ የሚችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።  

እአአ በ2015 ከኢራን ጋር የተደረሰውን የኒውክሌር ስምምነት ለማደስ የተጀመረው ድርድር ባለበት ቆሟል። የተጣለባትን ማዕቀብ ለማስነሳት ኢራን ከምዕራባውያን ጋር በተደረሰችው ስምምነት መሠረት የኒውክሌር እንቅስቃሴዋን ለመገደብ እና ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች እንዲገቡ ለመፍቀድ ተስማምታለች።

'ካሚካዜ ድሮኖች' ምንድናቸው?

·         ሻሄድ-136 የሚባል ኢራን መሳሪያ እንደተካተተ ይታመናል

·         እነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ከማድረሳቸው በፊት ዒላማው ላይ ያንዣብባሉ

·         ድሮኑ በፈንጂዎች የታጨቀ ሲሆን በሚፈለገው ቦታ ሲፈነዳ ድሮኑም ከጥቅም ውጭ ይሆናል

·         ብዙ ጊዜ በሞገድ የሚላክ ሲሆን በራዳር ለመለየትም አስቸጋሪ ነው።

·         20 ሺህ ዶላር የሚገመቱትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖች ኢራን ወደ ሩሲያ ለመላክ አቅዳለች ስትል አሜሪካ ትገልጻለች

·         በአሜሪካ የተሰራውን የስዊችብሌድ ሞዴልን ጨምሮ ዩክሬንም 'ካሚካዜ ድሮኖችን' ተጠቅማለች