የናይጄሪያ እስላማዊ ፖሊስ የማይጾሙ ሙስሊሞችን በቁጥጥር ስር አዋለ

ታትሟል

በናይጄሪያ ሰሜናዊ ግዛት በምትገኘው ካኖ የሚገኘው እስላማዊ ፖሊስ ሰኞ ዕለት በጀመረው የረመዳን ጾም ወቅት ምግብ ሲበሉ የታዩ 11 ሙስሊሞችን በቁጥጥር ስር አዋለ።

ካኖ የተሰኘችው ግዛት አብዛኛው ማህበረሰቧ ሙስሊም ሲሆን የእስላማዊ ህግ ስርዓት (ሻሪያ) ከዓለማዊ ህግ ጋር በአንድ ላይ ይሰራበታል።

ሂስባህ በመባል የሚታወቁት እስላማዊ ፖሊሶች በየዓመቱ በረመዳን ጾም በምግብ ቤቶች እና የገበያ ስፍራዎች ላይ ፍተሻዎችን ያካሂዳሉ።

በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት 10 ወንዶች እና አንዲት ሴት ሆን ብለው ጾም እንደማያፈርሱ ቃል ከገቡ በኋላ ተፈትተዋል።

“ማክሰኞ እለት ከምትሸጠው ኦቾሎኒ እየበላች የነበረች ሴት ጥቆማ የደረሰን ሲሆን እሷን ጨምሮ 11 ሰዎች ጾም ሽረው በልተዋል” ሲሉ የሂስባህ ቃለ አቀባይ ላውል ፋጌ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“የተቀሩት 10 ወንዶች በከተማዋ ውስጥ እንቅስቃሴዎች በሚበዛባቸው ገበያዎች አቅራቢያ ተይዘዋል” ብለዋል።

ቃለ አቀባዩ የፍተሻ ስራው እንደሚቀጥል ገልጸው ነገር ግን ይህ የእስልምና እምነት ተከታይ ያልሆኑትን እንደማይመለከትም ተናግረዋል።

“የእስልምና ተከታዮች ያልሆኑትን አናስርም ምክንያቱም ይህ አይመለከታቸውም። ወንጀል ፈጽመዋል ብለን የምናምነው መጾም ላለባቸው ሙስሊሞች ምግብ አብስለው መሸጣቸውን ካወቅን ነው” ሲሉም አክለዋል።

በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት ግለሰቦች ከአሁን በኋላ ጾም እንደማይሽሩ ቃል ከገቡ በኋላ የተፈቱ ሲሆን “አንዳንዶቹም ክትትል እንዲደረግባቸው ቤተሰቦቻቸውን፣ ዘመዶቻቸውን ማግኘት ነበረብን” ሲሉም አስረድተዋል።

የእስልምና እምነት ተከታዮች ከፍተኛ ቁጥር ባለባቸው 12 የናይጄሪያ ሰሜናዊ ግዛቶች ሸሪዓ ከሌላኛው ዓለማዊ ህግ ጋር አብሮ እንዲሰራም ተግባራዊ የሆነው ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ነው።

ረመዳን በእስልምና የዘመን አቆጣጠር ዘጠነኛው ወር የአረብኛ ስም ነው። ከጨረቃ ዑደት ጋር ተያይዞ የረመዳን ቀን የሚጀመርበት ዕለት በየዓመቱ ይለያያል። የዘንድሮውም ጾም መጋቢት 2/ 2016 ተጀምሯል።

የረመዳን ወር የእስልምና ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው ቁርዓን ለነብዩ መሐመድ የተገለጠበትን ጊዜ የሚዘክር ነው።

ከእስልምና አምስት አምዶች አንዱ የሆነው የረመዳን ወር፤ በፆም እና በጸሎት የሚታሰብ ሲሆን፣ ሕዝበ ሙስሊሙ ይህን ወር የእምነቱን ሥርዓት ጠብቆ እንዲያሳልፈው ይጠበቃል።

በረመዳን የፆም ወቅት በመላው ዓለም የሚገኙ ሁሉም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች፤ ፀሐይ ወጥታ እስክትጠልቅ ድረስ ከማንኛውም ዓይነት ምግብ እና መጠጥ ይቆጠባሉ።