የዓለም የምግብ ዋጋ ለተከታታይ አምስት ወራት መቀነሱን የፋኦ መረጃ አመለከተ

ሰብል የሚያጭድ ትራክተር

የፎቶው ባለመብት, NURPHOTO / GETTY

የምስሉ መግለጫ, የዩክሬንን ወደቦች ለመክፈት የተደረሰው ዓለም አቀፍ ስምምነት ብዙ ሰብሎች ወደ ዓለም አቀፍ ገበያዎች እንዲደርሱ አስችሏቸዋል።
ታትሟል

የተባበሩት መንግሥታት በዓለም ዙሪያ ባደረገው ጥናት ለተከታታይ አምስት ወራት የምግብ ዋጋ ቅናሽ መታየቱን አመለከተ።

ይህም በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ያለው የኑሮ ውድነት ላይ ጫና ከሚያሳድሩ ችግሮች አንዱ ሊቀንስ እንደሚችል ማሳያ ነው ተብሏል።

መረጃው እንዳለው በነሐሴ ወር የዋጋ ጠቋሚው ወደ 138 የቀነሰ ሲሆን፣ አሁን ላይ ደግሞ ሩሲያ ዩክሬንን ከመውረሯ በፊት ከነበረው ጊዜ ዝቅ ማለቱን አሳይቷል።

ሩሲያ እና ዩክሬን የሱፍ ዘይት፣ በቆሎ እና ስንዴን ጨምሮ ሌሎች የምግብ ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩ ዋነኛ አገራት ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እንዳለው ሐምሌ ወር ላይ በድርጅቱ የተደገፈውና የዩክሬን ወደቦች እንዲከፈቱ የተደረሰው ስምምነት የጥራጥሬ እና የአትክልት ዘይት ዋጋን ቀንሷል።

ይህም ማለት ተጨማሪ ምርቶች ወደ ዓለም አቀፍ ገበያው ገብተዋል ማለት ነው።

የፋኦው ኢሪን ኮሌር፣ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የምግብ ዋጋ መቀነስ ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው።

“የጥራጥሬ ምርት አቅርቦት ችግር በዚህ ዓመት ለተከሰተው የምግብ ዋጋ መናር ዋነኛው መንስዔ ሆኖ ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ አቅርቦቶች እየጨመሩ ነው” ብለዋል ኮሌር።

ለዚህም ምክንያቱ በተለይ በካናዳ፣ በአሜሪካ እና በሩሲያ ያለው ምርት የተሻለ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል። እነዚህ ሦስት አገራት ዋነኛ የስንዴ ላኪዎች ናቸው።

በሌሎች ምግቦች ላይም ምግቦችን ወደ ውጪ ለመላክ የነበረው ገደብ በመቅለሉ የስኳር እና የዘይት ዋጋ እንዲቀንስ የረዳ ሲሆን፣ በሌሎች ምርቶች ላይ ያለው ፍላጎት መቀነስም የሥጋ እና የወተት ተዋፅኦ ውጤቶች ዋጋ እንዲቀንስ አድርጓል ብለዋል።

ኢንዶኔዥያ የፓልም ዘይት የውጪ ንግድ ቀረጥን በጊዜያዊነት በመቀነሷም የምግብ አምራቾች በብዛት ለሚጠቀሙት የአትክልት ዘይት ተጨማሪ አማራጭ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

በምግብ ዋጋ የሚከሰት ግሽበት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የምግብ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚከሰት የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ነው።

በዚህ ሳምንት ዩሮዞን በነሐሴ ወር ዓመታዊ የዋጋ ግሽበቱ 9.1 በመቶ መድረሱን አስታውቋል። ለዚህ የዋጋ ግሽበት ምክንያቱ አንዱ ኢነርጅ (ኃይል) ሲሆን አሃዙም 38.3 በመቶ ነበር።

ነገር ግን ያልተቀነባበሩ ምግቦች በ10.9 በመቶ ግሽበት ተመዝግቦባቸው ከኃይል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ነበር የተቀመጡት።

በቅርቡ በዩናይትድ ኪንግደም እና በአሜሪካ የታየው የዋጋ ግሽበት መረጃ ተመሳሳይነት ታይቶበታል።

የፋኦ መረጃ፣ በወተት ተዋፅኦ፣ ሥጋ እና ስኳር ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ መታየቱን አመልክቷል።

የከብት እና ሌሎች የእንስሳት ምርቶች ዋጋ በግንባር ቀደምትነት ወደ ውጪ በሚላኩባቸው አገራት ውስጥ ባለው ደካማ ፍላጎት ምክንያት ቀንሷል።

ለዚህ ምን አልባት ሸማቾች ወደ ርካሽ አማራጮች ፊታቸውን እያዞሩ መሆኑን እንደሚያመላክት ፋኦ ጠቁሟል።  

የኢዲ ኤንድ ኤፍ ማን የግብርና ምርቶች ድርጅት የምርምር ኃላፊ ኮና ሃቅ እንዳሉት፣ የምጣኔ ሐብት ውድቀቱ አሳሳቢነት እያደገ በመምጣቱ እንደ በቆሎ፣ የአትክልት ዘይት እና ሌሎች ምርቶች ፍላጎት ይወድቃል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

ሆኖም ኮሌር፣ አሁን ባለው የአቅርቦት ሰንሰለት ችግር እና ለውጡ እንዲመጣ በሚወስደው ጊዜ ምክንያት ሁሉም አገራት የዋጋ መቀነሱን ወዲያውኑ ሊመለከቱት አይችሉም ብለዋል።

የፋኦ መረጃ እንደሚያሳየው መጋቢት ወር ላይ ከፍተኛ ሆኖ ከተመዘገበው 159.7 በመቶ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ቢሆንም ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ግን አሁንም በ10 ነጥብ ከፍ ያለ ነው።

በአውሮፓ የተከሰተውን የሙቀት ማዕበል እና በፓኪስታን የተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅን በመጥቀስም የአየር ሁኔታ በምግብ ሰብል ዋጋ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ መጨመሩን ኮሌር አስረድተዋል።

ወደፊት የሚገጥሙ ተግዳሮቶች

በዚህ ሳምንት የዩክሬን የግብርና ሚኒስትር ማይኮላ ሶልስኪ፣ በጦርነቱ ምክንያት በመጪዎቹ ምርቶች ላይ ጉዳት እንደሚደርስ አስጠንቅቀዋል።

ለሚቀጥለው ዓመት ምርት ስንዴ እና ገብስ የሚዘራባቸው ቦታዎች በሩሲያ ወረራ ምክንያት 20 በመቶው እንዲቀንስ ሆኗል። የዩክሬን ግብርና ምክር ቤት በበኩሉ ድጋፎች በመጥፋታቸው ምርት እንደሚቀንስ አሳውቋል።

ኮሌር በበኩላቸው አሁን ላይ በዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ መቀነስ ከታየ በኋላም ቢሆን በ2011 ከታየው በላይ ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

“ለዚህም በርካታ ምክንያቶች አሉ። አንዱ የኢነርጂ ዋጋ መጨመር ሲሆን ይህም የማዳበሪያ ዋጋ መናርን  እንዲሁም የአቅርቦት አለመረጋጋትን ያስከትላል” ብለዋል።

“ምንም እንኳን የተወሰኑት የዩክሬን ወደቦች ቢከፈቱም ጊዜያዊ ነው የሚሆነው፣መጠኑም ቢሆን አነስተኛ ነው ። በመሆኑም የምግብ ዋጋን ይበልጥ ለመቀነስ እንዲረዳ ይህንን መጠን መጨመር ያስፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል።