በናይጄሪያ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ600 በላይ ሰዎች ሞቱ

በናይጄሪያ የተከሰተ የጎርፍ አደጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ በአስር ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነው በተባለለት የጎርፍ አደጋ ከ600 በላይ ሰዎች ሕይወት አለፈ።

በጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋው 1.3 ሚሊዮን ሰዎች ሲፈናቀሉ ከ200,000 በላይ ቤቶች ደግሞ ወድመዋል።  

የጎርፍ መጥለቅለቁ እስከ ህዳር 2015 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

በቅርቡ በናይጄሪያ የተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ "አስደንጋጭ" አደጋ ከመሆን ባለፈ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ብዙ ግዛቶች በቂ ዝግጅት አለማድረጋቸውን የአገሪቱ የአደጋ መከላከል ሚኒስትር ተናግረዋል።

ናይጄሪያ በየጊዜው የጎርፍ መጥለቅለቅ ቢያጋጥማትም የዘንድሮው ግን ከወትሮው በእጅጉ የከፋ ነው ተብሏል።

መንግሥት ከወትሮው በተለየ የጣለው ከባድ ዝናብ እና የአየር ንብረት ለውጥ ለችግሩ ተጠያቂ ናቸው ብሏል።

የዝግጅትና የመሠረተ ልማት አለመሟላት ጉዳቱን እንዳባባሰው ባለሙያዎች ያክላሉ።

በጎርፍ መጥለቅለቁ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ወድመዋል።

የበሽታው መስፋፋት ስጋትም ተፈጥሯል። የምግብ እና የነዳጅ አቅርቦቶችም ተስተጓጉለዋል።

የናይጄሪያ የሰብዓዊ ጉዳዮች እና የአደጋ አስተዳደር ሚንስትር ሳዲያ ኡመር ፋሩክ እሑድ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ባለስልጣናት በጣም ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን እንዲያስወጡ ጠይቀዋል።

ባለሥልጣናቱ ለተጎጂዎች የምግብና ሌሎች ድጋፎችን እያደረጉ ነውም ብለዋል።

“የተቀናጁ ጥረቶች” እና ቅድመ ማስጠንቀቂያዎች ቢሰጡም ብዙ የክልል መንግሥታት ለአደጋው “አልተዘጋጁም” ብለዋል።

የጎርፍ አደጋው በናይጄሪያ ከሚገኙ 36 ግዛቶች 27ቱን አዳርሷል።

የናይጄሪያ ምጣኔ ሐብት ባለፈው አንድ ዓመት የተቀዛቀዘ ሲሆን የዋጋ ግሽበት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ በማለቱ ብዙዎች ከኑሮ ጋር ግብግብ ገጥመዋል።  

የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት ባለፈው ወር እንደገለጹት ናይጄሪያ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ከተጋረጠባቸው ስድስት ሃገራት መካከል አንዷ ነች።

የናይጄሪያ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የጎርፍ አደጋው እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ይቀጥላል ብሏል። እንደ አናምብራ፣ ዴልታ፣ ወንዞች፣ ክሮስ ሪቨር እና ባዬልሳ ባሉ የሃገሪቱ ደቡብ አንዳንድ ግዛቶች ችግሩ ሊቀጥል እንደሚችል አስጠንቅቋል።