ከወንድሙ ጋር በቁጥጥር ስር የዋለው እንዳልካቸው ዘነበ ይግባኝ ጠየቀ

በአርትስ ቲቪ ላይ የሚተላለፈውን 'አበስኩ ገበርኩ' የተሰኘ ዝግጀት አቅራቢ የሆነው እንዳልካቸው ዘነበ

የፎቶው ባለመብት, Endalkachew Zenebe

ታትሟል

በአርትስ ቲቪ ላይ የሚተላለፈውን 'አበስኩ ገበርኩ' የተሰኘ ዝግጀት አቅራቢ የሆነው እንዳልካቸው ዘነበ እና ታናሽ ወንድሙ ተከተል ዘነበ ላይ የወረዳ ፍርድ ቤት የፈቀደውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የዞኑ ፍርድ ቤት ዛሬ በቀረበለት ይግባኝ መሰረት እንደሚመለከተው ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ገለጹ።

ጋዜጠኛው እንዳልካቸው በማኅበራዊ ድረ ገጹ፣ በትውልድ ቀዬው ምዕራብ አባያ ወረዳ ብርብር ከተማ ካለ ፍርድ ቤት መጥሪያ እንደደረሰው እና ወደ አካባቢው በመጓዝ ፍርድ ቤት በፈቃዱ እንደሚቀርብ ከሦስት ቀናት በፊት ገልጾ ነበር።

ወላጅ እናቱ ወ/ሮ መስከረም ይልማ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ምንም እንኳን የደረሰው መጥሪያ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ሐሰተኛ መረጃን በማሰራጨት መጠርጠሩ ቢጠቀስም፣ ግልጽ ጥፋቱ ምን እንደሆነ እንዳላወቁ ተናግረዋል።

"በእርግጥ መጥሪያው በፌስቡክ ላይ ያጋራው፣ የብርብር ከተማ ከንቲባ የሆኑት ሰላም ቦዳ ወንድም ነው። ወንድምህ ፌስቡክ ላይ ከንቲባዋን ተሳድቧል፤ አንተም እሱን ላይክ እና ሼር አድርገሃል ብለው ነው" ሲሉ ወላጅ እናቱ ተናግረዋል።

ሁለት ልጆቻቸው አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ እና የጊዜ ቀጠሮው ሊሰጥ አይገባም በሚል አርባ ምንጭ ለሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም. ይግባኝ ማለታቸውን ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ ለወረዳው ፖሊስ እና ይግባኝ ባዮች መጥሪያ መስጠቱን እና ዛሬ ከሰዓት ጉዳያቸው እንደሚታይ እንደተነገራቸው ወላጅ እናቱ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

እንዳልካቸው ዘነበ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ነዋሪነቱ በአዲስ አበባ እንደሆነ እና መጥሪያውንም ያደረሰው ሕጋዊ አካል እንደሌለ እናቱ ተናግረዋል።

ነገር ግን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተመለከተውን ይህንን መጥሪያ ተከትሎም ወደ አካባቢው ተጉዞ እጁን መስጠቱን ተናግረዋል።

የደረሰው መጥሪያ ላይም ብሔርን ከብሔር ያጋጫል የሚል ወንጀላ መጠቀሱን ብሎም በእንዳልካቸው ላይ ደግሞ ላይክ እና ሼር አድርገሃል የሚል መኖሩን ተናግረዋል።

እንዳልካቸው በጄቲቪ፣ አፍሪ ኸልዝ የቴሌቪዢን ጣቢያዎች የሰራ ሲሆን አሁን በአርትስ ቲቪ ላይ የራሱን ሾው እያዘጋጀ ያስተላልፋል።