ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሕንድ የባቡር ግጭት ከሞቱ ሰዎች መካከል 80ውን አስክሬኖች መለየት አልተቻለም
ከአምስት ቀናት በፊት በተከሰተውና በሁለት አስርት ዓመታት ግዜ የከፋው ነው በተባለው የሕንድ የባቡር አደጋ ከሞቱ 288 ሰዎች መካከል 80 የሚሆኑትን ሰዎች አስክሬን መለየት እንዳልተቻለ ተገለጸ።
የበርካታ የሟቾችን አስክሬን የሚወስድ ቤተሰብ ጠፍቷል እንዲሁም በጉዳት ምክንያት አካላቻው ክፉኛ የተጎዱ ማንነታቸውን ለመለየት አስቸጋሪ የሆኑ አስክሬኖችን የተለያዩ ሰዎች የቤተሰብ አባሌ ነው ብለው ለመውሰድ ጥረት አድርገዋል።
ኦዲሻ በተባለው ግዛት የተሳፋሪዎችና አንድ የእቃ ባቡር ተጋጭተው ነው አደጋው የተከሰተው።
ከ1,000 በላይ ሰዎች ተጎድተው ሆስፒታል ገብተዋል። አሁንም ቤተሰቦቻቸውን እየፈለጉ ያሉ ሰዎችም አሉ።
የግዛቱ ዋና ጸሐፊ ፕራዲፕ ጄን 288 ሰዎች እንደሞቱና 83 አስክሬኖችን መለየት እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
ተሳፋሪዎች የጫነው ባቡር ሀዲድ ስቶ እቃ ከጫነ ባቡር ጋር ተጋጭቷል። ሌላ የተሳፋሪዎች ባቡር በተቃራኒው አቅጣጫ እየተጓዘ ነበር።
በሁለቱ ባቡሮች 3,000 ተሳፋሪዎች እየተጓዙ ነበር። ሁለቱም ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በኦዲሻና በሌሎችም ግዛቶች ያሉ ነዋሪዎች ቤተሰቦቻቸውን ፍለጋ በየሆስፒታሉ እየዞሩ መረጃ እየጠየቁ ነው።
ከሞቱ ሰዎች መካከል አስክሬናቸውን መለየት ያልተቻለ እንዳሉም ተገልጿል።
ሙሐመድ ኒዛሙዲን የተባሉ ግለሰብ የልጅ ልጃቸውን አስክሬን ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
የ16 ዓመቱ ታፍሲር አንሳሪ እና የ13 ዓመት ወንድሙ ታውሲፍ ከአባታቸው ጋር እየተጓዙ ነበር።
አባታቸውም እስካሁን አልተገኘም። የልጆቹ ምሥል ሕይወታቸው አልፎ በሆስፒታል ላይ ከተለጠፉት መካከል ነው።
ፊታቸው በአደጋው ምክንያት እንዳልነበረ ሆኗል። አያታቸው ግን እነሱ መሆናቸውን ለማወቅ ችለዋል። አስክሬናቸው ግል አልተሰጣቸውም።
“የልጅ ልጆቼ ፊት መቼ ጠፋኝ” ብለዋል አያትየው።
የሰዎችን ምሥል እና ማንነት በማመሳከር ሥራ ያሉት ቪጄ አመሩታ ኩላንግ “የፎቶ ስብስቡን ስትመለከቱ ሰዎቹ ማንነታቸውን መለየት በሚያስቸግር ሁኔታ መጎዳታቸውን ታያላችሁ” ብለዋል።
የዘረ መል ምርመራ በማድረግም የሰዎችን ማንነት ለመለየት እየተሞከረ ነው።
ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች አስክሬን ለአስር ቀናት ሆስፒታል ቆይተው ከዚያ አስክሬናቸው እንደሚቃጠል ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ንሬንድራ ሞዲ አደጋው የደረሰበትን ቦታ ጎብኝተው ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው “በጽኑ እንደሚቀጣ” ገልጸዋል።
አንደኛው ጉዳት የደረሰበት ሃዲድ ማስተካከያ ተደርጎበታል።
በቀን ከ12,000 በላይ ሰዎች በባቡር የሚጓጓዙባት ሕንድ በዓለም በባቡር ትስስር ግንባር ቀደም ከሆኑ አገራት አንዷ ናት።
ይህ ወቅት ሰዎች በብዛት በባቡር የሚጓጓዙበት ሲሆን የሕንድ ባቡር ሃዲድ መሠረተ ልሟት እምብዛም ጥሩ አይደለም።