ጉዳፍ ጸጋይ በ5ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆነች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካዋ ኦሪገን እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሴቶች 5 ሺህ ሜትር የፍፃሜ ውድድር ጉዳፍ ፀጋይ ወርቅ ባለቤት ሆናለች።
ጉዳፍ በዚህ ድሏ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ያገኘቻቸውን የወርቅ ቁጥሮች አራት ማድረስ ችላለች።
ከፍተኛ ፉክክር በነበረበት ውድድር ጉዳፍ 14፡46: 29 በመግባት ነው ባለክብር የሆነችው።
ኬንያዊቷ ቢትሪስ ቺቤት ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን በቅታለች።
ሌላኛው ኢትዮጵያዊት ዳዊት ስዩም ሦስተኛ በመውጣት የነሃስ ሜዳሊያ አስገኝታለች።
ለድሉ መሳካት ትልቅ ድርሻ የነበራት ለተሰንበት ግደይ አምስተኛ በመውጣት አጠናቃለች።
ለተሰንበት በዚሁ የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወሳል።
ከእኩለ ሌሊት በኋላ በተካሄደው የ5ሺህ ሜትር ውድድር የመጨረሻዎቹ 100 ሜትሮች ድረስ አሸናፊዋን መለየት አስቸጋሪ የሆነበት ነበር።
በ1500 ሜትር ልምድ ያላት ጉዳፍ ትንቅንቁን የኋላ ኋላ በበላይነት አጠናቃለች።
ጉዳፍ ከወራት በፊት በ1500 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ክብረ ወሰኑን መስበሯ ይታወሳል።
በኦሪገኑ ውድድርም ከቀናት በፊት በዚሁ ዘርፍ ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን በቅታለች።
ጉዳፍ ከውድድሩ በኋላ “በመጎዳቴ ምክንያት የቶክዮው ኦሎምፒክ በጣም ከባዱ ጊዜ ነበር” ማለቷን ወርልድ አትሌቲክስ አስነብቧል።
“ለ1500 ሜትር በደንብ ስዘጋጅ ቆይቻለሁ። ይህም በጨረሻዎቹ ሜትሮች ላይ በፍጥነት እንድሄድ ጠቅሞኛል። ሲፋን ትልቅ እና እሷም የ1500 ሜትር አትሌት መሆኗን አውቃለሁ። ስለዚህ እሷም ፍጥነቱ አላት። እሷ ስትቀደም እኔ ፍጥነቴን በመጨመር ሜዳሊያውን ለማግኘት በቅቻለሁ” ብላለች።
ዳዊት በበኩሏ ከዓመታት የጉዳት ቆይታ በኋላ ነው ወደ ድል የተመሰለችው።
“የሜዳሊያ አሸናፊ ሆኜ መድረክ ላይ ለመውጣት ተስፋ አድርጌያለሁ” ትላለች ዳዊት።
“በዚህ ዘርፍ የሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን አልሜያለሁ። ለአምስት ዓመታት ከጉዳት ጋር ስታገል ቆይቻለሁ። ስለዚህ ይህ ድል ለእኔ ልዩ ነው” ብላለቸ።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በእስካሁን ቆይታ አራት የወርቅ፣ አራት የብር እና ሁለት የነሃስ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
በኦሪጎን እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጠናቀቃል።
ኢትዮጵያ ሜዳሊያ የምትጠበቅብትን የወንዶች 5000 ሜትርን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎችም ቀሪ ውድድሮችን ታከናውናለች።












