“ከእረፍት መልስ ጨዋታችን ተቀባይነት የሌለው ነበር፤ ይቅርታ መጠየቅ አለብን” ሚኬል አርቴታ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፣ ትናንት እሁድ አርሰናል በብራይትን የገጠመው የ3 ለ 0 ሽንፈት በቡድኑ ተጫዋቾች ዘንድ ለፕሪሚዬር ሊጉ ዋንጫ የነበራቸው ተስፋ ማብቃቱን የሚያመለክት ነው።
ነገር ግን አሁንም አንዳንድ የአርሰናል ደጋፊዎች የማይጨበጥ በሚመስል ተስፋ ላይ ዐይናቸውን ጥለዋል። መሪው ማንችስተር ሲቲ ቀጣይ የሚኖሩት ጨዋታዎችን ከተሸነፋ እና አርሰናል ሁሉንም ማሸነፍ ከቻለ ከሳምንታት በፊት ቡድኑ የነበረውን ዋንጫው ተስፋ ሊመልሰው ይችላል።
አርሰናል የገጠመው ሽንፈት ተቀናቃኙ ሲቲ በአራት ነጥብ መሪነቱን እንዲያጠናክር አደርጎታል። የመሪው የፔፕ ጓርዲዮላ ቡድን በቀጣይ እሁድ በራሱ ሜዳ ከቼልሲ ጋር በሚኖረው ጨዋታ በአሸናፊነት ከወጣ ዋንጫውን በድጋሚ ማንሳቱን ያረጋግጣል።
“እውነቱን ለመናገር ሁኔታው አሁን ለእኛ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። በጣም ፈታኝ ነው” ሲል የአርሰናል አምበል ማርቲን ኦዲጋርድ ለስካይ ስፖርትስ ተናግሯል።
ከብራይተን ጋር ከተደረገው ጨዋታ በኋላ እንደተናገረው “ጥሩ ስሜት ላይ አይደለሁም። በተለይ ከእረፍት በኋላ የነበረን ጨዋታ ጥሩ አልነበረም፤ እውነቱን ለመናገር ቡድናችን ውስጥ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም።
“አሁን ምንም ተስፋ እንደሌለ ነው የሚሰማኝ።”
በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ የነበረው አርሰናል ከእረፍት መልስ በስድስተኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠረባቸው ግብ የሽንፈታቸውን በር ከፍቶታል።
ከዚያ በኋላ የተቆጠሩት ግቦችም አርሰናል ባለፉት ሳምንታት እየተዳከመ የመጣውን ከሁለት እስርት ዓመታት በኋላ የሊጉን ዋንጫ የማንሳት ተስፋውን የበለጠ እንዲጨልም አድርጎታል።

የፎቶው ባለመብት, arsenal
የአርሰናሉ አሰልጣኝም ድክመታቸውን በይፋ ከመቀበል ወደኋላ አላሉም።
“ከእረፍት መልስ በነበረን አጨዋወት ምክንያት ይቅርታ መጠየቅ አለብን። ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነገር ነበር” ብሏል ሚኬል አርቴታ።
ጨምሮም “በስሌት ከሄድን ዋንጫውን ለማንሳት የሚየስችል ተስፋ አለ፤ ነገር ግን አሁን ስለዚያ ለማሰብ አይቻልም። ከእረፍት መልስ ስለነበረው ጨዋታችን እና ስለውጤቱ መለስ ብለን መገምገም አለብን” ብሏል።
በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ማንችስተር ሲቲ ያለፈተና ኤቨርተንን ጉዲሰን ፓርክ ላይ 3 ለ 0 ሲያሸንፍ ወደ ዋንጫው የመቅረብ ተስፋውን አጠናክሯል።
እሁድ ምሽት በነበረው ጨዋታ ከእረፍት መልስ የአርሰናል ብቃት እና አጨዋወት በርካታ ደጋፊዎቹን አስቆጥቷል። በስታዲየሙ ታድመው ከነበሩት ደጋፊዎች መካከልም ብዙዎች ጨዋታው ከመጠናቀቁ በፊት በንዴት አቋርጠው ለመውጣት ተገደው ነበር።
አብዛኛውን የውድድሩን ጊዜ በደረጃው ሰንጠረዥ ላይ በመሪነት ተቀምጦ የነበረው አርሰናል፤ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ዋንጫውን ሊያነሳ እንደሚችል ትልቅ ተስፋን ፈጥሮ ነበር።
ኋላ ላይ ቀስ በቀስ እየጣለ የመጣቸው ነጥቦች እና የተፎካካሪው የማንችስተር ሲቲ ኃያል እየሆነ መምጣት የቡድኑን ዋንጫ የማንሳት ተስፋ ፈትኖት ቆይቷል። ነገር ግን ውድድሩ ወደ መጠናቀቂያው እየተቃረበ ሲመጣ የአርሰናል የነጥብ ልዩነት እየጠበበ ሲቲ መሪነትን ለመቆናጠጥ በቅቷል።
ይህም በደጋፊዎቹ ዘንድ ንዴት እና ቁጭት ቢፈጥርም ወደ ዋንጫ ተስፋው የመመለስ ዕድሉ ግን አልተሟጠጠም ነበር። የእሁድ ምሽቱ የብራይተን ሽንፈት በቡድኑ ደጋፊዎች ዘንድ የነበረውን ተስፋ አሟጦታል። በቡድኑ ውስጥም ይኸው ስሜት እየተንጸባረቀ ነው።
አርሰናል በብራይተን የገጠመው ሽንፈት ዋንጫውን ከእጃቸው ከማስመለጡ በሻገር በቡድኑ ውስጥ ጉልህ ጥያቄን አስነስቷል። ይህ ሽንፈት ምን ይዞ እንደሚመጣ በቀጣይ ቀናት የሚታይ ይሆናል።
ቡድኑ ከፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ላይ እጁ ቢነሳም፣ አርሰናል ከስድስት ዓመት በኋላ ዋደ ቻምፒየንስ ሊግ የመመለሱ ነገር እንደ ማስተዛዛኛ ሊታይ ይችላል።
የወቅቱ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ሊያበቃ አርሰናል ሁለት ጨዋታዎች ሲቀሩት መሪው ሲቲ ሦስት ይቀረዋል። በመጪው የሳምነቱ ማብቂያ ላይ ከቼልሲ ጋር በሚኖረው ጨዋታ ሲቲ ካሻነፈ የዋንጫ ባለቤትነቱን ያረጋግጣል።












