የዝውውር ጭምጭምታ፡ የኬን፣ ዛሃ እና ምባፔ መዳረሻ የት ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, EPA
የጀርመኑ ባየርን ሙኒክ ሃሪ ኬንን ለመግዛት የተሻሻለ ገንዘብ ሊያቀርብ ቢሆንም ቶተንሃም ግን አይቀበለውም ይላል የሜል ዘገባ።
ሙኒክ የ29 ዓመቱን እንግሊዛዊ አጥቂ ለመግዛት 70 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።
ሃሪ ኬን ከቶተንሃም ጋር ያለው ውል ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ይቀረዋል።
እንደ ጋርዲያ ዘገባ ከሆነ ቼልሲ የ30 ዓመቱን ቤልጂየማዊ ሮሜሎ ሉካኩ ለመሸጥ 40 ሚሊዮን ፓውንድ ይጠይቃል።
ተጫዋቹ በሳዑዲ አራቢያው አል ሂላልና በጣሊያኑ ጁቬንቱስ ይፈለጋል። ኢንተር ሚላን ሉካኩን ለመግዛት ያቀረበው ገንዘብ ውድቅ ሆኗል።
ፉትቦል ትራንስፈርስ እንዳስነበበው ማንቸስተር ዩናይትድ ከ20 ዓመቱ ዴንማርካዊ አጥቂ ጋር ከስምምነት ደርሷል።
ራስመስ ሆይላንድ ለአታላንታ የሚጫወት ሲሆን ክለቡ ከ60 ሚሊዮን ፓውንድ በታች አልቀበልም እያለ ነው።
ቶተንሃም ኢቫን ፔሪሲችን ለመተካት የቼልሲውን ስፔናዊ የግራ መስመር ተጫዋች ማርክ ኩኩሬያ ላይ ዓይናቸውን ጥለዋል።
ስካይ ስፖርትስ እንደዘገበው ስድስት የፒኤስጂ ተጫዋቾች በኪሊያን ምባፔ ጉዳይ ቅሬታ እንደገባቸው ለክለቡ አሳውቀዋል።
በቅርቡ ክለቡን የተቀላቀሉ ሁለት ተጫዋቾችን ጨምሮ ስድስት የፈረንሳዩ ክለቡ ተጫዋቾች፤ ምባፔ ስለክለቡ የሚሰጠው አስተያየት ተገቢ አይለም ይላሉ።
ቼልሲ የ22 ዓመቱን አሜሪካዊ አጥቂ ፎላሪን ባሎጉን ከአርሰናል ለማስመጣት ድርድር መጀመራቸውን ሜል አስነብቧል።
አይቮሪ ኮስታዊው የክንፍ መስመር ተጫዋች ዊልፍሬድ ዛሃ ከክሪስታል ፓላስ ጋር የገባው ውል ቢጠናቀቅም አዲስ ውል ሊያኖር እንደሚችል ጋርዲያን ፅፏል።
የፈረንሳዩ ፒኤስጂ፣ የጣሊያኑ ናፖሊ እና የቱርኩ ጋላታሳራይ ዛሃን ማስፈረም የሚፈልጉ ክለቦች ናቸው።
ባየርን ሙኒክ የውል ማፍረሻ 50 ሚሊዮን ዩሮ ከፍሎ ደቡብ ኮሪያዊው ኪም ሚን-ጄን ከናፖሊ ሊያስመጣ እንደሆነ የጀርመኑ ስካይ ስፖርት ዘግቧል
የ26 ዓመቱ ኪም ወደ ባየር ሙኒክ ከመጣ እስከ 2028 የሚያቆየውን ውል ያኖራል።
ካሜሩናዊውን ግብ ጠባቂ ለማንቸስተር ዩናይትድ ሊሸጡ ነው እየተባሉ ያሉት ኢንተር ሚላኖች የባየር ሙኒኩን ያን ሶመር ለማስፈረም እንደፈለጉ የዘገበው የስካይ ስፖርትስ የጀርመን ክንፍ ነው።
ወደ ፕሪሚዬር ሊግ ያደገው በርንሊ የቦሩሲያ ዶርትመንዱን ተከላካይ ሶማይላ ኩሊባሊ በውሰት ለማስመጣት መስማመቱ ተሰምቷል።
በሌላ በኩል ፉልሃም ከብራዚላዊው የክንፍ መስመር ተጫዋች ዊሊያም ጋር አዲስ ውል ሊገባ አወንደሆነ ፉትቦል ኢንሳይደር ፅፏል።












