ሊቨርፑል ከ ማድሪድ፡ ታላቁ የአውሮፓ እግር ኳስ ፍልሚያ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
ዛሬ ምሽት አራት ሰዓት ላይ የፈረንሳይዋ ዋና ከተማ ፓሪስ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ የኃያላኑን ሪያል ማድሪድና ሊቨርፑል ፍልሚያ ታስተናግዳለች።
ሁለቱ ቡድኖች ከአራት ዓመታት በፊት በዚሁ መድረክ ለፍጻሜ ተገናኝተው ማድሪዶች ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው።
እግር ኳስ የሚወድ ማንኛውም ሰው ይህ ጨዋታ እንዲያመልጠው አይፈልግም። እግር ኳስ ለምኔ የሚሉት እንኳን ስለነዚህ ቡድኖች ፍልሚያ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሰምተዋል።
በአውሮፓ ቻምፒየንስ ታሪክ ዋንጫውን 13 ጊዜ በማንሳት ተወዳዳሪ የሌላቸው ማድሪዶች ስድስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ መሆን ከቻሉት ሊቨርፑሎች ጋር ነው የሚፋለሙት።
የስፔን ኃያላኑ ማድሪዶች በዘንድሮው ውድድር ከምድብ ድልድል ጀምሮ አበቃላቸው እየተባለ ነው እዚህ የደረሱት።
ቼልሲን፣ ፒኤስጂን እንዲሁም ለዋንጫው ለማለፍ ደግሞ ማንቸስተር ሲቲን ባለቀ ሰዓት ባስቆጠሯቸው ግቦች በመታገዝ ነው እዚህ የደረሱት።
አጥቂው ካሪም ቤንዜማ ከምን ጊዜው በበለጠ በምርጥ አቋም ላይ ይገኛል። በዘንድሮው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ 15 ግቦችን በማስቆጠር ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ቤንዜማ፣ በስፔን ላሊጋም ቢሆን 27 ግቦችን በማስቆጠር ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ነው የጨረሰው።
ሌላኛው የቡድን አጋሩ ቪኒሺየስ ጁኒየርም ቢሆን እንደ ዘንድሮ ብዙ ግቦችን አስቆጥሮ አያውቅም። በዛሬው ምሽት ጨዋታ እነዚህ ኮከቦች የሊቨርፑልን የተከላካይ መስመር በእጅጉ እንደሚፈትኑ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል የሊቨርፑሉ አምበል ጆርዳን ሄንደርሰን በስታ ዴ ፍራንስ ስታዲየም “ማድሪድን ዝም እናሰኛለን” ሲል ተደምጧል። በዘንድሮው ውድድር ኤፍኤ ካፕ እና ካራባዎ ካፕ ያሸነፉት ሊቨርፑሎች በፕሪምየር ሊጉ ዋንጫውን በማንቸስተር ሲቲ ተነጥቀዋል።
አራት ዋንጫ ለማሸነፍ አልመው የነበሩት አሰልጣኙ የርገን ክሎፕ አሁን ላይ የመጨረሻ ተስፋቸው ቻምፒየንስ ሊግ ሆኗል።
የርገን ክሎፕ ስለቡድናቸው ስብስብ ሲናገሩ ይህ ቡድን በእውነት ልዩ ነው ብለዋል። ዋንጫውን አሸንፈው ደጋፊዎቻቸውን በደስታ ለማስፈንጠዝ መዘጋጀታቸውን አክለዋል።
ስለጨዋታው ተጠይቆ የነበረው የማድሪዱ ቤንዜማ ሊቨርፑሎች ምናልባት ይህንን ዋንጫ ያሸነፉ ያህል ሊያስቡ ይችላሉ። እኛም እሱን ነው የምንፈልገው ብሏል።
አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ በበኩላቸው የዓመታት ልምድ ባላቸው ሞድሪች እና ክሩዝ የሚመራው የመሀል ሜዳው ቤንዜማ እና ቪኒሺየስ ሲጨመሩበት ቡድናቸው አስፈሪ እንደሚሆን ዝተዋል።
ከአራት ዓመት በፊት ሊቨርፑል በማድሪድ በፍጻሜው ሲሸነፍ ተጎድቶ የወጣው ሞሐመድ ሳላህ በዚህ ፍልሚያ ግብ ማስቆጠር እንደሚፈልግ ተናግሯል። ማድሪድ ለዋንጫው ማለፉን ሳያረጋግጥ በፊት እንኳን በፍጻሜው ማድሪድን መግጠም እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ ተናግሮ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ሊቨርፑል ከ ማድሪድ የሚያደርጉት ጨዋታ ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከአራት ዓመታት በፊት እአአ 2018 ሁሉቱ ኃያል ቡድኖች ለፍጻሜ ተጋጥመው ነበር።
በጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ የሊቨርፑሉ ኮከብ ሞ ሳላህ የተፈጸመበትን ጉዳት ተከትሎ ከሜዳ ወጣ። ይህም ለሊቨርፑል ትልቅ ጉዳት ነበር።
ከዚያም የሊቨርፑሉ ግብ ጠባቂ ሎሪስ ካሪየስ ቡድኑን ትልቅ ዋጋ ያስከፈሉ ሁለት ጥፋቶችን ሰራ። የመጨረሻም ማድሪድ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ሊቨርፑልን መርታት ቻለ።
ሊቨርፑሎች ዛሬ ቅዳሜ ምሽት ግን ሌላ ቀን ነው እያሉ ነው።
የእንግሊዙ 'ዴይሊ ሜይል ኦንላይ' ከሊቨርፑል አምበል ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ በስፋት አስነብቧል። ጆርዳን ሄንደርሰን በስታ ዴ ፍራንስ ስታዲየም “ማድሪድን ዝም እናሰኛለን” ብሏል።
የሊቨርፑሉ አሰልጠኝ የርገን ክሎፕ ደግሞ በቡድናቸው ስብስብ መተማመን እንዳላቸው ለቢቢሲ ብሬክፋት ተናግረዋል።
ክሎፕ “ይህ ቡድን በእውነት ልዩ ነው” በማለት የቡድን አባሎቻቸውን አሞካሽተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማድሪድ ልዩ አቋም ላይ ይገኛል። ጎል አዳኙ ካሪም ቤንዜማ ከመቼም ጊዜ በላይ ድንቅ አቋም ላይ ነው።
ማድሪድ ከእዚህ የፍጻሜ ውድድር የደረሰው በፒኤስ ጂ፣ ቼልሲ እና ማንችስተር ሲቲ ቀድሞ የተያዘበትን ብልጫ ቀልብሶ ነው።
የስፔኑ እውቅ ጋዜጣ 'ማርካ' ቤንዜማን በፊት ገጽ አውጥቶታል።
ለማድሪዱ አሰልጣኝ አንቼሎቲም ቢሆን የነገው ጨዋታ ሊቨርፑልን የሚበቀሉበት አጋጣሚን ይፈጥርላቸዋል። እአአ 2005 ላይ በቱርክ ኢስታንቡል በነበረው የቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታ፣ ሊቨርፑል ከኤስ ሚላን መገናኘታቸው ይታወሳል።
በዚያ ጨዋታ ሊቨርፑል 3ለ0 ከመመራት ተነስቶ ኤስ ሚላንን ሲያሸንፍ አንቼሎቲ የኤስ ሚላን አሰልጣኝ ነበሩ።
በነገው ጨዋታ ደግሞ ከ90ኛው ደቂቃ በኋላ ሊቨርፑል የበላይነቱን ይዞ ያጠናቅቃል የሚለው ግምት ሚዛን ደፍቷል።
ሊቨርፑል 46 በመቶ የማሸነፍ ዕድል ተሰጥቶታል። ሪያል ማድሪድ ሊቨርፑልን ሊረታ የሚችልበት አጋጣሚ ደግሞ 28 በመቶ የተገመተ ሲሆን፣ 26 በመቶ ጨዋታው ከ90ኛው ደቂቃ መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱ ቡድኖች አቻ ይሆናሉ ተብሎ ተገምቷል።












