በሕንድ አንድ ታዳጊ በኒፓህ ቫይረስ መሞቱን ተከትሎ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሕንዷ ኬራላ ግዛት የጤና ባለስልጣናት አንድ የ14 ዓመት ታዳጊ በኒፓህ ቫይረስ መሞቱን ተከትሎ ማስጠንቀቂያ አወጡ።

እንደግዛቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ገለጻ 60 ሰዎችም ለበሽታው በጣም ተጋላጭ ከሆኑ ምድብ ውስጥ መሆናቸው ተለይቷል።

የኬራላ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ቬና ጆርጅ፤ ታዳጊው ከፓንዲካድ ከተማ የመጣ መሆኑን እና ከእርሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ተለይተው ምርመራ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ ጭምብል ማድረግ እና ሆስፒታል ያሉ ሰዎችን ከመጠየቅ መቆጠብ የመሳሰሉ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ኒፓህ ቫይረስ እንደ አሳማ እና የሌሊት ወፍ ካሉ እንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ይገልጻል።

በተጨማሪም በተበከለ ምግብ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በመገናኘት ሊተላለፍ ይችላል።

የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱን ወረርሽኝን የመቀስቀስ አቅም ስላለው ቅድሚያ የሚሰጠው በሽታ እንደሆነ ገልጿል።

ቫይረሱ በ2018 ለመጀመሪያ ጊዜ ከተመዘገበበት ጊዜ ወዲህ በኬራላ ግዛት በደርዘን ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል ተብሏል።

የ14 ዓመቱ ታዳጊ በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠ ከአንድ ቀን በኋላ እሑድ ዕለት ሕይወቱ ማለፉን የሕንድ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።

የኬራላ ክፍሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቫይረሱ በጣም ከተጋለጡ አካባቢዎች አንዷ ናት ተብሏል።

ባለፈው ዓመት ሮይተርስ ይፋ ባደረገው ምርመራ እንዳረጋገጠው በኬራላ ፈጣን የከተሜነት መስፋፋት እና ፈጣን የደን ምንጠራ መኖሩ "እንደ ኒፓህ ያለ ቫይረስ እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታዎችን" ይፈጥራል ብሏል።

በደን መመናመን ምክንያት እንስሳት ከሰው ጋር ተቀራርበው መኖራቸው ቫይረሱ ከእንስሳት ወደ ሰው እንዲተላለፍ ምክንያት እንደሚሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የግዛቱ መንግሥት የኒፓህ ወረርሽኝን ለመከላከል አቅድ እያዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል።

ባለፈው ዓመት በኬራላ ግዛት አምስት ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች እና ቢሮዎች ተዘግተው ነበር።