ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን ከዓመታት በኋላ በሳዑዲ የሚገኘው ኤምባሲዋን ዳግም ከፈተች
የመካከለኛው ምሥራቅ ተቀናቃኞች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ካቋረጡ ከሰባት ዓመታት በኋላ ኢራን በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ከፍታለች።
ኤምባሲው በሪያድ ዳግም ሲከፈት የኢራን እና የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች መገኘታቸውን የሳዑዲ መንግሥት ቴሌቪዢን ጣቢያ ዘግቧል።
የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊሪዛ ቢጋድሊ የኤምባሲው ዳግም ሥራ መጀመር በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ትብብር “ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን” ያመለክተ ነው ብለዋል።
ሁለቱ የባሕረ ሰላጤ አገራት ቻይና ባመቻቸችው ውይይት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ወደ ነበረበት ለመመለስ ከተስማሙ ከሦስት ወራት በኋላ ነው ኤምባሲው የተከፈተው።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ሳዑዲ ታዋቂውን የሺአ ሙስሊም መምህር በሞት መቅጣቷን ተከትሎ ነው ኤምባሲዋን የዘጋችው።
የሳዑዲ ድርጊትን በመቃወም በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ኢራን ውስጥ የሚገኘው ኤምባሲዋ ላይ ወረራ ከተፈጸመ በኋላ ከኢራን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተቋርጧል።
ባለፈው አርብ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆስኒ አሚር አብዶላሃያን ከሳዑዲው አቻቸው ልዑል ፋይሳል ቢን ፋራን አል ሳዑዲ ጋር ደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን በተገናኙበት ጊዜ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻል እያሳየ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልዑል ፋርሃን ሳዑዲ በቴህራን የሚገኘውን ኤምባሲዋን ዳግም ለመክፈት ሥራ መጀመራቸውን እና በቅርቡም ጉብኝት እንደሚያደርጉ ማረጋገጣቸውን ገልጿል።
ራሷን የሱኒ ሙስሊሞች መሪ አድርጋ በምትቆጥረው ሳዑዲ አረቢያ እና ከፍተኛ የሺአ ሙስሊሞች መገኛ በሆነችው ኢራን መካከል ቀጠናዊ የበላይነትን ለመያዝ አስርት ዓመታትን የፈጀ ፍትጊያ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የሁለቱ አገራት ፍትጊያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚካሄድ የእጅ አዙር ጦርነት ይፋ ወጠወቷል።
በየመን ሳዑዲ አረቢያ ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ ከመንግሥት ጎን የቆሙ ኃይሎችን ስትደግፍ፣ ከሁቲ አማጽያን በተጻጻራሪ ቆማለች።
የሁቲ አማጽያን በሳዑዲ ከተሞች እና የነዳጅ ጣቢያዎች በድሮን እና በሚሳኤል ድብደባ የፈጸመችባቸውን መሳሪያዎች ያስገባችው ኢራን ነች ብትባለም ስታስተባብል ቆይታለች።
በተጨማሪም ሳዑዲ አረቢያ ኢራን በሊባኖስ እና ኢራቅ እጇን አስገብታለች ስትልም ትከሳለች። በሁለቱ አገራት ውስጥ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች ሰፊ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ተጽእኖ አላቸው።
ታጣቂዎቹ በባሕረ ሰላጤ ዕቃ ጫኝ መርከቦች እና የነዳጅ ማመላለሻዎችን የደበደቡ ሲሆን፣ እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 በሳዑዲ አረቢያ ወሳኝ የነዳጅ መሠረተ ልማት ላይ ከተፈጸመው የሚሳኤል እና የድሮን ድብደባ ጀርባ እንዳሉ ይታመናል።
ሆኖም ኢራን በመርከቦችም ሆነ በነዳጅ መሠረተ ልማቶች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ውስጥ “እጄ የለበትም” ብላለች።
በሪያድ ያላው የሳዑዲ ኤምባሲ ከመከፍቱ ቀደም ብሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንተኒ ብሊንከን በሳዑዲ ጉብኘት አድርገው ነበር።
ኃላፊው በሳዑዲ ቆይታቸው ከመሪዎች ጋር ስለኢራን፣ ስለ ነዳጅ ዋጋ፣ በቀጠናው ስላለው የቻይና እና የሩሲያ ተጽእኖ እንዲሁም ሳዑዲ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስን በተመለከተ ይወያያሉ ተብሎ ይጠብቅ ነበር።