ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ የፍልስጤም ፓስፖርት የያዙ በርካታ ሰዎችን ቪዛ አገደች
የአሜሪካ ባለስልጣናት የፍልስጤም ፓስፖርት ለያዙ ሁሉም የጉብኝት ቪዛ አመልካቾች ቪዛ ማገዳቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
ይህ እርምጃ የተሰማው በኒውዮርክ ከሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ በፊት 80 የፍልስጤም ባለስልጣናት ቪዛ ከተከለከሉ በኋላ ነው።
በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ከፍልስጤም የጋዛ ግዛት ወደ አሜሪካ ለመጓዝ የሚፈልጉ ሰዎች የጎብኚ ቪዛዎች መስጠት ቆሞ ነበር።
ይህ አዲስ የተሰማው እርምጃ እስራኤል በወረራ በያዘችው ዌስት ባንክ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ጨምሮ በርካቶችን ይመለከታል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ እርምጃውን መውሰዱን በግልጽ ባያረጋግጥም "የአሜሪካን ሕግ እና ብሔራዊ ደህንነታችንን ጋር በተጣጣመ መልኩ ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰድን ነው" ብሏል።
እርምጃውን በሚመለከት እአአ በነሐሴ18 ለኤምባሲዎች እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች መመርያ መሰጠቱን ኒው ዮርክ ታይምስ እና ሲኤንኤን ዘግበዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የቆንስላ ሠራተኞች ስደተኛ ላልሆኑ የፍልስጤም አስተዳደር ፓስፖርት የያዙ ሁሉም ሰዎች ቪዛ እንዲከለከሉ መታዘዛቸው ተጠቅሷል።
ይህ ውሳኔ ለተለያዩ ዓላማዎች ለንግድ፣ ለትምህርት ወይም ለሕክምና ወደ አሜሪካ ለመምጣት ለሚፈልጉ ፍልስጤማውያን ተግባራዊ ይሆናል።
በዚህ ውሳኔ መሠረት ባለሥልጣናቱ እያንዳንዱን አመልካች ተጨማሪ ፍተሻ እንዲያካሂዱ ይጠበቅባቸዋል፣ ይህም ለፍልስጤማውያን ቪዛ እንዳይሰጥ የጅምላ ክልከላ ነው ሲል ኒው ዮርክ ታይምስ በሪፖርቱ አክሎ ተናግሯል።
ሌሎች ፓስፖርቶችን በመጠቀም የቪዛ ማመልከቻ ማቅረብ የቻሉ ፍልስጤማውያን ምንም ዓይነት ችግር እንዳልገጠማቸው ተነግሯል።
ምንም እንኳ የትራምፕ አስተዳደር እስራኤል በጋዛ በሐማስ ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ በቁርጠኝነት ቢደግፍም ለዚህ ውሳኔ ያነሳሳው ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
ባለፈው ወር ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና ፈረንሳይን ጨምሮ በርካታ አገራት ለፍልስጤም መንግሥት በተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች እውቅና እንደሚሰጡ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ዋሽንግተን ይህንን ለመከተል ምንም እቅድ የላትም ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ፍልስጤምን በመደገፍ የሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎችን ነቅፏል።
እርምጃው ቀደም ሲል ከተወሰዱ ሁለት እርምጃዎችን በመከተል ፕሬዚዳንቱ በቪዛ ላይ ያላቸውን አቋም የበለጠ ማጠናከራቸውን ያሳያል።
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ በዚህ ወር መጨረሻ በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዳይሳተፉ ከተከለከሉት በርካታ የፍልስጤም ባለስልጣናት መካከል አንዱ ናቸው።
አሜሪካ የባለስልጣናቱን ቪዛ የሰረዘችው ፈረንሳይ እና ካናዳን ጨምሮ አንዳንድ አገራት በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለፍልስጤም አገርነት በይፋ እውቅና እንሰጣለን ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የፍልስጤም ባለስልጣናትን የሰላሙን ጥረት በማናጋት እንዲሁም "የአንድ ወገን የፍልስጤም ዕውቅናን በመሻት" ከሰዋቸዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እአአ ከነሐሴ 16 ጀምሮ በተለይ ከጋዛ ለሚመጡ ፍልስጤማውያን የጎብኚ ቪዛ መስጠቱን አቁሟል።
በዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪነት የተፈረጀው ሐማስ ጋዛን የሚያስተዳድር ሲሆን መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ደቡብ እስራኤልን አጥቅቶ 1,200 ሰዎችን ሲገድል 251 አግቷል።
ጥቃቱን ተከትሎ የእስራኤል ጦር መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረ ሲሆን ቢያንስ 63,459 ፍልስጤማውያን መሞታቸውን በሐማስ የሚመራ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
አሁን የዩናይትድ ስቴትስ የቪዛ ፖሊሲ ከዌስት ባንክ የሚመጡ ሰዎችን እና ሰፊ የፍልስጤም ዲያስፖራዎችን አካትቷል።
ስለእርምጃው የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ "የትራምፕ አስተዳደር የፍልስጤም ባለስልጣናት ፓስፖርት የያዙ ግለሰቦችን በሚመለከት ያስተላለፈው የቪዛ እገዳ የአሜሪካ ሕግን እና ብሔራዊ ደህንነታችንን ከግምት በማስገባት የተወሰደ ተጨባጭ እርምጃ ነው" ብለዋል።
"እያንዳንዱ የቪዛ ውሳኔ የብሔራዊ ደህንነት ውሳኔ ነው፤ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቪዛ ውሳኔዎችን የፍልስጤም አስተዳደር ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች እያጣራ እና ውሳኔዎችን እያሳለፈ ነው።"