ፕሬዝዳንት ባይደን ባለጸጎች ላይ ከፍተኛ ግብር የሚጥል ሕግ አጸኑ

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ጆ ባይደን በአየር ንብረትና በጤና ዙርያ የቀረቡ ረቂቅ ሕጎች ላይ ፊርማቸውን አኖሩ።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በፊርማቸው ያጸኑት ሕግ በሃብታሞች ላይ ጠንከር ያለ ግብር የሚጥል ነው።

ይህ ረቂቅ ሕግ ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ኩባንያዎች ላይ ግብር በመጣል በአየር ንብረት ለውጥና በጤና ዙርያ ለሚሠሩ ሥራዎች የሚውል ገንዘብ የሚያስገኝ እንዲሆን የተዘጋጀ ነው።

ባይደን ትናንት በረቂቅ ሕጉ ላይ ፊርማቸውን በማኖር ሕግ እንዲሆን አጽንተውታል።

ይህ ሕግ ከዚህ ወዲያ በጤና ዙርያ በሐኪም የሚታዘዙ መድኃኒቶች ዋጋ እንዲስተካከል የሚያደርግ ነው።

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ለዓመታት በሚታዘዙ መድኃኒቶች ዋጋ ላይ ቅናሽ እንዲደረግ ሲወተውቱ የቆዩትን ጥያቄ ይመልሳልም ተብሏል።

ዲሞክራቶች በዚህ ረገድ የሦስት ትሪሊዮን ዶላር ጥቅል ዕቅድ የነበራቸው ሲሆን ይህ አሁን በፕሬዝዳንቱ የተፈረመው ሕግ ግን ከዚህ የገንዘብ መጠን በእጅጉ ያነሰ ነው።

ይህ ሕግ ጆ ባይደን ወደ ሥልጣን ሲመጡ አደርጋቸዋለሁ ብለው ለደጋፊዎቻቸው ቃል ከገቧቸው ጉዳዮች አንዱና ዋንኛው ነበር።

ጆ ባይደን ይህን ረቂቅ ሕግ ማድረጋቸው ምናልባት በቅርብ ለሚካሄደው የአሜሪካ የአጋማሽ ምርጫ (ሚድተርም ኢሌክሽን) በመራጮች ላይ ተጽእኖ እንዲኖረው የታሰበ ነው የሚሉ አልጠፉም።

የአጋማሽ ዘመን ምርጫ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሥልጣን በያዘ በሁለተኛ ዓመት የሚደረግ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት የማሟያ ምርጫ ነው።

ይህ ምርጫ በመጪው ኅዳር ይደረጋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአጋማሽ ዘመን ምርጫው በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የዲሞክራቶች የበላይነት እንዲያበቃ ሊያደርግ ይችላል የሚል ግምት አለ።

ይህ ፕሬዝዳንቱ ትናንት ማክሰኞ ሕግ ያደረጉት ረቂቅ በውስጡ የአየር ንብረትና የጤና ዘርፎችን የያዘ ነው።

መጠኑም በድምሩ 700 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥን ለመታገል እና ለጤና ጥበቃ የሚውል ነው።

ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 375 ቢሊዮን ዶላሩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚውል መሆኑ በአሜሪካ ታሪክ ለዚህ ዘርፍ ከፍተኛ በጀት ተደርጎ ተወስዷል።

የአየር ንብረት ሳይንቲስቶች ይህ ገንዘብ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለውጥ እንዲመጣ ሊያደርግ ቢችልም ለውጡ ግን መጠነኛ ነው ብለዋል።

በዚህ ሕግ መሠረት አሜሪካ በተለያዩ መንገዶች ወደ ከባቢ የምትለቀው የበካይ ልቀት በፈረንጆቹ 2030 በ44 ከመቶ ዝቅ እንዲል ያስችላል።

ይህ ሕግ ግዙፍ ኩባንያዎች ወደ ከባቢ የሚለቁት በካይ ጋዝን እንዲቀንሱ የሚያስገድድ ባይሆንም ወደ ታዳሽ ኃይል ፊታቸውን ካዞሩ ግን የግብር እፎይታን ይሰጣቸዋል።

የኤሌክትሪክ መኪና የሚገዙ ሰዎች ብድርን ጨምሮ ቅናሽ እንዲሁም በተራዘመ ጊዜ ክፍያ እንዲፈጽሙ ያበረታታል። በቤት ውስጥ ቁሳቁሶች ምርት ላይ ኃይል ቆጣቢ ምርቶችን ለሚያቀርቡም ኩባንያዎችም ልዩ ማበረታቻን ያደርጋል።

ይህ ሕግ ከአየር ንብረት ለውጥ ሌላ በጤናው ዘርፍ አዲስ ቅናሽን ይዞ መጥቷል።

በተለይም እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ አሜሪካዊያን የታዘዙላቸውን መድኃኒቶች በቅናሽ እንዲያገኙ በጤና መድኅን በኩል መንግሥት ከመድኃኒት አቅራቢዎች ጋር እንዲደራደር ያስችለዋል።

ባይደን ይህን ረቂቅ ሲፈርሙ “ይህ ለአሜሪካ ታሪካዊ ቀን ነው” ያሉ ሲሆን ይህ ረቂቅ ሕግ እንዳይሆን እያንዳንዱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የሪፐሊካን አባል ተቃውሞት ነበር ብለዋል።

ይህ ሕግ በግዙፍ ኮርፖሬሽኖች ላይ ዝቅተኛው የግብር ወለል 15 በመቶ እንዲሆን ያዛል። ዓመታዊ ገቢያቸው ከ400ሺህ ዶላር በታች ለሆኑ ዜጎች የግብር ጭማሪን እንደማያስከትል ተነግሯል።

ይህ ሕግ የአገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤት በርካታ ተጨማሪ የግብር ወኪሎችን እንዲቀጥር የሚያስችለውን 46 ቢሊዮን ዶላር ያቀረበ ነው።

ይህ ሕግ ተፈጻሚነቱ በሁለት ዓመት ሊዘገይ ይችላል።

ረቂቁ ሕግ ለመሆን በተቃረበበት ጊዜም በርካታ በአሜሪካዊያን ሕይወት ላይ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው አንቀጾች እንዲወጡ ተደርገዋል።

ከእነዚህ መሀል የስኳር በሽተኞች ኢንሱሊን ለመግዛት በሚያወጡት ዋጋ ላይ የዋጋ ምጣኔ ያስቀምጥ የነበረው አንቀጽ ይገኝበታል።

ትሬቨር ሚልተን የ21 ዓመት ወጣት ነው። ይህ ረቂቅ ባለቀ ሰዓት እንዲወጡ በተደረጉ አንቀጾች ምክንያት ቅሬታን ፈጥሮበታል።

ከ12 ዓመቱ ጀምሮ የስኳር በሽተኛ የሆነው ትሬቨር በወር ለኢንሱሊን ብቻ 210 ዶላር ይከፍላል።

“ሁልጊዜም ሕይወቴን ለማቆየት 210 ዶላር መክፈል እንዳለብኝ ሳስብ እደነቃለሁ” ይላል።