ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ አፍሪካ ነጭ ተማሪ የጥቁር ተማሪ ንብረት ላይ መሽናቱ እያነጋገረ ነው
ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስቴሌንቦሽ የተሰኘ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አንድ ነጭ ተማሪ የሌላ ጥቁር ተማሪ ንብረት ላይ ሽንቱን ሸንቷል የሚል ክስ ከቀረበበት በኋላ ለጊዜው ከትምህርቱ መታገዱን ዩኒቨርሲቲው ለቢቢሲ አረጋገጠ።
ዩኒቨርሲቲው እንዳለው ክስተቱን ተከትሎ ፈጣን ምርመራ የተጀመረ ሲሆን ተማሪው ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ቤቱ ሊታገድና የወንጀል ክስ ሊመሠረትበትም ይችላል።
የስቴሌንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትናንት ሰኞ ዕለት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ በሰላማዊ ሰልፍ የጠየቁ ሲሆን ዩኒቨርሲቲውም ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ ገልጾላቸዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል በስፋት በተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል ነጩ ተማሪ የጥቁሩ ተማሪ ንብረቶች ላይ ሽንቱን ሲሸና የሚያሳይ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲውም ተማሪው ይህንን ያደረገው ከዘረኝነት በመነጨ ስሜት ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል።
የዩኒቨርሲቲው ቃል አቀባይ የሆኑት ማርቲን ቪልጆን ጉዳዩን አስመልከተው በሰጡት መግለጫ ላይ ተቋማቸው የተፈጠረውን ነገር በእጅጉ እንደሚኮንነውና ''ይህንን የማይጠቅም እንዲሁም ዘረኛ የሆነ ተግባር'' እንደሚቃወሙት ገልጸዋል።
ንብረቱ ላይ ጉዳት የደረሰበት ተማሪ እስካሁን ድረስ እንዳልተረጋጋና ምን እንደተፈጠረ ለመረዳት እየሞከረ እንደሆነ ተገልጿል።
የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው ጥቁሩ ተማሪ በተማሪዎች ማደሪያ ውስጥ ተኝቶ የነበረ ሲሆን ከእንቅልፉ ሲነቃ የሆነ ሰው ክፍሉ ውስጥ ነበር።
በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይም ጥቁሩ ተማሪ ነጩን ተማሪ ለምን ንብረቶቹ ላይ ሽንቱን እንደሚሸና ሲጠይቀው ይታያል።
ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል በስፋት መታየቱን ተከትሎ በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን በአገራቸው አሁንም ድረስ ስላልጠፋው ዘረኝነት መነጋገር ጀምረዋል።