ኢንዶኒዥያ የፓልም ዘይት ወደ ውጭ እንዳይላክ ማገዷ የአፍሪካ አገራትን አስጨንቋል

የፎቶው ባለመብት, other
በዓለም ከፍተኛ መጠን ያለው የፓልም ዘይትን ወደ ውጭ ከሚልኩ አገራት ቀዳሚዋ የሆነችው ኢንዶኒዢያ የአገር ውስጥ ፍጆታዋን ለማርካት በሚል በምርቱ ላይ የውጭ አገዳን ጥላለች፡፡
ኢንዶኒዥያ በተለይ በአገሯ የምግብ ዘይት ዋጋ መናር ስላሳሰባት ማንኛውም የምግብ ዘይት መሥሪያ የሚሆን ጥሬ የሰብል ምርቶች ላልተወሰነ ጊዜ ለውጭ ገበያ ዝግ ሆነው እንዲቆዩ ጥብቅ መመሪያን አስተላልፋለች፡፡
ይህ ሁኔታ ብዙ የአፍሪካ አገራትን አሳስቧል፡፡
አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ርካሽ የሆነው የፓልም ዘይት ተጠቃሚ ናቸው፡፡
አፍሪካ ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት ብቻ በድምሩ በገንዘብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት፣ በመጠኑ 4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚሆን የፓልም ዘይት ከኢንዶኒዢያና ማሌዢያ አስገብታለች፡፡
የኢንዶኒዥያ የፓልም ዘይት ዕቀባ የመጣው በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት የተነሳ የሱፍ አበባ ዘይት ገበያ መናጋቱን ተከትሎ ነው፡፡
ዩክሬን በዓለም ቁጥር አንድ የሱፍ አበባ ዘይት አምራችና ላኪ አገር ነበረች፡፡ በየዓመቱ 5 ሚሊዮን ቶን ለዓለም ታቀርብ ነበር፡፡
ራሺያ በበኩሏ የዓለምን 25 ከመቶ የሱፍ ዘይት ምርት የምትሸፍን አገር ነበረች፡፡
አሁን ላይ ኢንዶኒዥያ በፓልም ዘይት ላይ የጣለችው የውጭ ንግድ ዕቀባ ለአፍሪካ ነዋሪዎች ትልቅ ራስ ምታት እንደሚሆን ተፈርቷል፡፡
በተለይ ከዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ የዋጋ ግሽበት መከሰት፣ ብሎም የነዳጅና የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መናር ትልቅ ፈተና በሆነበት ወቅት የዘይት እጥረት መከሰቱ ነገሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገዋል ተብሏል፡፡
የፓልም ዘይት የተለያዩ የአትክልት ዘይቶችን ለማዘጋጀት የሚረዳ ሲሆን ከርሱ ሌላ ለጽዳትና የመዋቢያ ምርቶች መሥሪያነት ይውላል፡፡
አሁን ሕንድ፣ ባንግላዴሽና ፓኪስታን የፓልክ ዘይትን ከማሌዥያ በብዛት ማስገባት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡
ይሁንና የዓለም 2ኛዋ የፓልም ዘይት አምራች ማሌዥያ የኢንዶኒዥያን ያህል ምርት የማቅረብ አቅም የላትም፡፡ ይህም በዋናነት በሠራተኛ እጥረት የሚከሰት ነው፡፡
ኢንዶኒዥያ ለምሳሌ የሕንድን ፍላጎት በግማሽ ብቻ ነው መሸፈን የምትችለው፡፡ ፓኪስታንና ባንግላዴሽ በበኩላቸው 80 ከመቶ የሚሆነውን የፓልም ዘይት ፍላጎታቸውን ከኢንዶኒዥያ ያገኛሉ፡፡
ዕቀባው ዕድልን ይዞ ይመጣ ይሆን?
ኮኒ ማጎሙ በኡጋንዳ የናሽናል ፓልም ኦይል ፕሮጀክት ኃላፊ ነው፡፡ እሱ እንደሚለው ዕቀባው አፍሪካዊያን የፓልም ዘይትን በራሳቸው እንዲያመርቱ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡
‹‹አንደኛ በመሬት አጠቃቀም ደረጃ ለምርት የተመቸ ነው፤ ከማንኛውም ሰብል የበለጠ በትንሽ ቦታ ብዙ ምርት ይሰጣል፡፡ ሁለተኛ ለድህነት ቅነሳ አስፈላጊ ሰብል ነው፡፡ አንድ ጊዜ በ3 ዓመት ተኩል ዕድገቱን ከጨረሰ በኋላ በየ10 ቀናት ምርት መሰብሰብ ይቻላል፡፡ ይህም ለ25 ዓመታት ይዘልቃል›› ይላል፡፡
ኡጋንዳን የፓልም ዘይትን በአገር ውስጥ ለማምረት እየጣረች ያለች አገር ስትሆን ራሷን በምርቱ ለመቻል ቢያንስ 100ሺህ ሄክታር መሬት ምርት ያስፈልጋታል፡፡
በአፍሪካ ይህ ዕድል ካላቸው አገራት ውስጥ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ አይቮሪስት፣ ሴራሊዮን፣ ቡሩንዲና ታንዛኒያ ይጠቀሳሉ፡፡
ናይጄሪያ በ60ዎቹ የዓለም ቁጥር-1 የፓልም ዘይት አምራች የነበረች አገር ናት፡፡ ባለፈው ዓመት ግን ጠቅላላ ምርቷ 1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ብቻ ነበር፡፡
በተመሳሳይ ወቅት ኢንዶኒዥያ 44.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን አምርታለች፡፡
የኢንዶኒዥያን የውጭ ንግድ ዕቀባ ተከትሎ ስፔን፣ ቱርክ፣ ጀርመንና ዩኬ በአንዳንድ ዕመደብሮች ዘይት ለሁሉም በፍትሃዊነት እንዲዳረስ በሚል በነፍስ ወከፍና በቤተሰብ የተወሰነ ምርት ብቻ መሸጥ መጀመራቸው የችግሩን ጥልቀት የሚያሳይ ነው፡፡












