የአሜሪካ ሴኔት ጥቁሯ ዳኛ የጠቅላይ ፍርድ ቤት አባል እንዲሆኑ ማረጋገጫ ሰጠ

ታትሟል

የዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት ዳኛ ኬታንጂ ብራውን ጃክሰንን ዘጠኝ አባላት ወዳሉት ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚካተቱ ካረጋገጠ በኋላ ፍርድ ቤቱ በ 233 ዓመታት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ጥቁር ዳኛ ሊያገኝ ነው ተብሏል።

ከዴሞክራቶች በተጨማሪ ሦስት ሪፐብሊካኖች ሹመቱን በመደግፍ 53 ለ 47 በሆነ ድምጽ ውሳኔውን አጽድቀዋል።

የጃክሰን ሹመት የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ጥቁር ሴት ለፍርድ ቤቱ ለማቅረብ የገቡትን ቃል ያሟላ ሆኗል።

ዴሞክራቱ ቻክ ሹመር ውሳኔውን ለአሜሪካ "የደስታ ቀን" ሲሉ ገልጸውታል።

የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ካማላ ሃሪስ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን መርተዋል።

የ51 ዓመቷ ዳኛ በሰኔ ወር በጡረታ የሚገለሉትን ዳኛ ስቴፈን ብሬየርን ይተካሉ።

ሹመቱ የዕድሜ ልክ በመሆኑ ጃክሰን ለብዙ አሥርተ ዓመታት በኃላፊነት ላይ እንዲቆዩ ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም በፍርድ ቤቱ 6 ለ 3 የሆነውን የወግ አጥባቂዎችወ የድምፅ ብልጫ ሚዛን የሚቀይር አይሆንም።

ጃክሰን ጉዳዮችን ለመወሰን "ዘዴ" እንዳላቸው ተናግረዋል። በመሥራቾቹ እንደሚታሰበው ሕገ መንግሥቱን ማክበር አስፈላጊ ስለመሆኑ ከሪፐብሊካን ሴናተሮች ጋር እንደሚስማሙም አስታውቀዋል።

በውሳኔው ወቅት ዴሞክራቶች የህዝብ አጋር ሆነው የመሥራት ልምዳቸውን ገልጸዋል። ከመጀመርያው የፍርድ ቤቱ ጥቁር ዳኛ ቱርጎድ ማርሻል በመቀጠል የወንጀል ተከሳሾችን በመወከል የስራ ልምድ ያላቸው የመጀመሪያዋ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ሆነዋል።

የዋሽንግተን ዲሲ ተወላጅ የሆኑት የሕግ ባለሙያዋ ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆነው የዲሲ አካባቢ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውስጥ እያገለገሉ ነው። ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በአንድ ወቅትም የሃርቫርድ የህግ መጽሔት አዘጋጅ ሆነው አገልግለዋል።

በጓንታናሞ የሚገኙ የሽብር ተጠርጣሪዎችን በመወከል ፍርድ ቤት በመቆማቸው አንዳንድ ሪፐብሊካኖች በወንጀል ጉዳይ ስስ ናቸው ሲሉ ጃክሰን ከሰዋል።

ሌሎች ደግሞ የሕግ ልምዳቸው ለፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ትልቅ ልምድ አድንቀዋል።

አዲሷ ዳኛ "በፍርድ ቤት ካላቸው ልምድ አንጻር ጥቂቶች ሊያገኙ የሚችሉትን ልምድ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይሰጣሉ" ብለዋል የአላስካው ሴናተር ሊዛ ሙርኮቭስኪ።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በአሜሪካያንዊ ህይወት ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ነው። በአብዛኛውም በግዛቶች እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ከፍተኛ አከራካሪ ህጎች እና አለመግባባቶች ዙሪያ የመጨረሻውን ውሳኔ ይሰጣል።