ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈረንሳዩ ማክሮን የዩክሬንና የሩሲያን ፍጥጫ ማርገብ እንደሚቻል ተናገሩ
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ላለመግባት ስምምነት መድረስ የማይቻልና ሩቅ ነገር እንዳልሆነ ተናገሩ።
ማክሮን ጨምረው ሩሲያ የደኅንነት ስጋት እንዳለባት ማሳሰቧ ተገቢ ነው ብለዋል።
ማክሮን ይህን ያሉት ዛሬ ሰኞ ቀጠሮ ከተያዘላቸውና ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ከመነጋገራቸው ቀደም ብሎ በሰጡት ቃለ ምልልስ ነው።
ማክሮን በምዕራቡና በሩሲያ መካከል አዲስ ሚዛን መፍጠር ያስፈልጋል፤ የአውሮጳ አገራትን ፍላጎትና የሩሲያን ፍላጎትም ማጣጣም ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ኾኖም ኢማኑኤል ማክሮን በሁለቱ ወገኖች ዘንድ ሚዛን ለማስጠበቅ ሲባል የዩክሬን ሉዓላዊነት ጉዳይ ለጥያቄ ይቀርባል ማለት እንዳልሆነ አስምረውበታል።
ሩሲያ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ድንበር ማስጠጋቷ ከተገለጸ ወዲህ በአካባቢው የጦርነት ስጋት እንዳንዣበበ አለ።
ሞስኮ አደጋው እንዲቀለበስ በርከት ያሉ ቅድመ ኹኔታዎችን ያቀረበች ሲሆን ከእነዚህ ዋናው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ወይም በምህጻሩ ኔቶ፣ ዩክሬንን አባል እንዳያደርግ የሚጠይቅ ነው።
ሞስኮ የኔቶ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በተለይም በምሥራቅ አውሮጳ በእጅጉ እንዲቀንስም ትፈልጋለች።
ምዕራባውያን አገራት ደግሞ ይህን የሩሲያን ፍላጎት ቸል በማለት በኒውክሊየር መሣሪያ ቅነሳ ላይ ማተኮርን መርጠዋል።
ማክሮን ለጆርናል ዱ ዲማንቼ ጋዜጣ እንዳሉት የሩሲያ ዋናው ፍላጎት ዩክሬንን በወረራ መያዝ ሳይሆን ኔቶ ዩክሬንን እንደ አባል እንዳያቅፋት ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ማክሮን ጨምረው ነገሩን ለማረገብ ከፑቲን ጋር የሚያደርጉት ውይይት በቂ እንደሚሆን፣ ፑቲንም በሰፊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ዝግጁና ግልጽ እንደሚሆኑላቸው ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ማክሮን ትናንት እሑድ ከባይደን ጋር በስልክ መነጋገራቸውንና የሩሲያ የደኅንነት ስጋት ቢሰማት ተገቢ እንደሆነ ለባይደን እንዳስረዷቸውም ተዘግቧል።
ማክሮን ዛሬ ወደ ሞስኮ ከዚያም ወደ ኪየቭ ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የማክሮን በዲፕሎማሲው እንዲህ ጎልቶ መውጣት በሚያዝያ ወር ለሚደረገው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አንዳች አንድምታ ይኖረዋል ይላሉ ተንታኞች።
ማክሮን የአውሮጳ ኅብረት ከሩሲያ ጋር አዲስ ቃል ኪዳንና አዲስ ግንኙነት እንዲኖር መነጋገር እንደሚገባና ኅብረቱ የሩሲያን ጉዳይ በዋሺንግተን ላይ መጣል እንደማያስፈልገው ጥቆማ ሰጥተዋል።
ይህ በእንዲህ ሳለ የአሜሪካ መንግሥት ሩሲያ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ በየትኛውም ቅጽበት ዩክሬንን ልትወር እንደምትችል አሁንም እያስጠነቀቀ ይገኛል።
ሁለት ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት ሩሲያ ዪክሬንን ለመውረር የሚያስፈልጋትን 70 ከመቶ ወታደራዊ ሎጂስቲክ ወደ ድንበር አስጠግታ በተጠንቀቅ ላይ ናት።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህን ይበሉ እንጂ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ግን የወረራ ስጋቱ አሜሪካ እንደምትለው የገነነ አይደለም።
ሚኒስትሩ ትናንት እሑድ በትዊተር ሰሌዳቸው "የምጽአት ቀን የደረሰ እንደሆነ የሚነገረውን ነገር አትመኑ፤ በሁለቱ ዋና ከተሞች መሀል ያለው ስሜት ፍጹም ከዚህ የተለየ ነው፤ ይሁንና አገራችን ዩክሬን ማንኛውም ጥቃት ለመመከት በተጠንቀቅ ላይ ናት።" ብለዋል።
አሜሪካ ባለፈው ሳምንት የሩሲያ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ዩክሬንን ለመውረር በቂ ሰበብ እንዲሆን በሚል ሐሰተኛ ፊልም ለመቅረጽ እንዳሰበ ደርሼበታለሁ ስትል ነበር።
ይህ ሐሰተኛ ፊልም የሩሲያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ተሰንዝሮ አስክሬናቸው በግላጭ እንዲታይ የሚያደርግና የሩሲያዊያንን ስሜት የሚኮረኩር እንዲሆን ዝግጅት እንደተደረበት አሜሪካ ይፋ አድርጋ ነበር።
ሆኖም እስከአሁን ይህን አሜሪካ ደረስኩበት ያለችውን ነገር የሚያመላክት ማስረጃ አልተገኘም።
ይህ በምዕራብ አገራትና በሩሲያ መሀል አዲስ ፍጥጫ የመጣው ሩሲያ የክሬሚያን ደቡባዊ ባሕረ ገብ ከወረረች ከ8 ዓመት በኋላ መኾኑ ነው።