ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አልሻባብ ሞቃዲሾ ውስጥ ዛሬ በፈጸመው የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት 8 ሰዎች ተገደሉ
በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በመኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ አማካይነት በተፈጸመ የቦንብ ጥቃት ስምንት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ፖሊስ መግለጹን የአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን አስታወቀ።
ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ በሚገኝ ትምህርት ቤት የሚማሩ 13 ልጆችን ጨምሮ 17 ያህል ሰዎች በፍንዳታው የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በአልሻባብ አጥፍቶ ጠፊ አሽከርካሪነት ጥቃቱን የፈጸመው ፈንጂዎች የተጫነበት መኪና ኢላማው አድርጎት የነበረው ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደኅንነት ጥበቃ አገልግሎት የሚሰጥን 'ዱጉፍ' የተባለን የግል የጥበቃ ድርጅት የተሽከርካሪዎች አጀብን ነበር።
በጥቃቱ የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞ ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ፖሊስ ያለው ነገር የለም።
ሞቃዲሾ ውስጥ የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የፍንዳታ ጥቃቱ የተፈጸመው በርካታ ሕዝብ በሚንቀሳቀስበት የከተማዋ ክፍል ጠዋት ላይ ነው።
ጥቃቱ በሞቃዲሾ ከተማ ውስጥ ከባድ ፍንዳታ እንዲሰማ ያደረገ ሲሆን በመጀመሪያ ላይ የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ አባላት ላይ የተነጣጠረ እንደሆነ ተዘግቦ ነበር።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ስፍራ የሚገኘው ትምህርት ቤት የተወሰኑ ከፍሎች በፍንዳታው ምክንያት ውድመት የደረሰባቸው ሲሆን ከቆሰሉት መካከል አብዛኞቹ ተማሪዎች መሆናቸውን የዜና ምንጮች እየዘገቡ ነው።
ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው የሶማሊያው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ጥቃቱን ስለመፈጸሙ አረጋግጧል። የቡድኑ ደጋፊ የሆኑ የመረጃ ምንጮች እንዳሉት የቡድኑ ጥቃት ኢላማ ያደረገው "ነጭ ወታደረዊ መኮንኖችን" ነው ብለዋል።
ታጣቂ ቡድኑ አልሻባብ የፀጥታ ኃይሎችንና የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናትን በተደጋጋሚ ኢላማ በማድረግ ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።