ቢሊየነሩ ሰር ሪቻርድ ብራንሰን ራሳቸው ባስገነቧት ሮኬት የጠፈር ጫፍ ደርሰው ተመለሱ

ታትሟል

እንግሊዛዊው ቢሊየነር ሰር ሪቻርድ ብራንሰን የተሳካ ጉዞን ወደ ጠፈር አድርገው ተመልሰዋል።

ይህን የሆነው የራሳቸው ኩባንያ ለ17 ዓመታት ሲያስገነባት በነበረች ሮኬት ነው። ይህች ሮኬት ቨርጂን ጋላቲክ ዩኒቲ ትባላለች።

ይህን የሳቸውን የተሳካ የጠፈር ጉዞን ተከትሎ ወደ ሕዋ መዝለቅ ተራ የቱሪዝም ጉዳይ ሊሆን ተቃርቧል።

ከአሜሪካ ኒው ሜክሲኮ ግዛት ተነስታ ሽቅብ የተምዘገዘገችው ቨርጂን ጋላቲካ ሮኬት 17 ዓመታት የተደከመባት ናት።

ቢሊየነሩ ሰር ሪቻርድ የጠፈርን ጫፍ ተጠግተው ወደ ምድር ከተመሰሉ በኋላ ይህ "በሕይወቴ ልዩ ተአምር ነው" ብለዋል።

ቢሊየነሩ ወደ ምድር የተመለሱት ምድርን ከለቀቁ ከአንድ ሰዓት በኋላ ነው።

‹ይህን ቅጽበት ገና ሕጻን እያለሁ አልመው ነበር። ነገር ግን ከጠፈር ሆኖ ምድርን ቁልቁል የማየት ስሜት ከልጅነቴ ጀምሮ ስላሰብኩትና ስላለምኩት የማያስደምመኝ መስሎኝ ነበር። ተሳስቻለሁ› ብለዋል።

‹ሁሉም ነገር እንደ ተአምር የሚቆጠር ነው› ያሉት ቢሊየነሩ በጠፈር የቱሪዝም ጉዞ በራሳቸው ኩባንያ ስኬታማ የሕዋ ጉዞ በማድረግ በዓለም የመጀመርያው አድርጓቸዋል።

ሌለኞቹ አሜሪካዊያን ቢሊየነሮች የአማዞን ጄፍ ቤዞስ እና የስፔስ ኤክሱ ኤለን መስክ ለተመሳሳይ ስኬት እየተሰናዱ እንደሆነ ይታወቃል።

ሰር ሪቻርድ ከምድር እርቀው የሄዱበት 53 ማይል ወይም 85 ኪሎ ሜትር ነው።

ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ግለሰቦችን ወደ ጠፈር ለቱሪዝም ለመላክ ዝግጅቱ ተጧጡፏል።

ወደ 600 ሰዎች ቀድመው ቀብድ የከፈሉ ሲሆን አንድ ተሳፋሪ በትንሹ ሩብ ሚሊዮን ዶላር የትኬት ወጪ ማድረግ ይኖርበታል።

ተጓዦቹ መሬትን ቁልቁል ማየት ከመቻላቸውም በላይ በዩኒቲ መንኮራኮር ውስጥ ደግሞ ለ5 ደቂቃ መንሳፈፍ ይፈቀድላቸዋል ተብሏል።

ሰር ሪቻርድ ይህን የጠፈር ቱሪዝም ሐሳብ የጸነሱት ከ17 ዓመታት በፊት ሲሆን ያን ጊዜ ተግባራዊ ጉዞ በፈረንጆቹ 2007 እንደሚጀመሩ ቃል ገብተው ነበር።

ሆኖም በርካታ ቴክኒካዊ እክሎች በማጋጠማቸውና በተለይም በ2014 በሙከራ ላይ የመከስከስ አደጋ በማጋጠሙ እስከ ትናንት ድረስ ሐሳቡ ዕውን ሳይሆን ቀርቷል፡፡

የዓለም ቢሊየነሮች አዲሱ ፋሽን ወደ ጠፈር የቱሪዝም ጉዞ መጀመር ሲሆን በዚህ ረገድ ጄፍ ቤዞስ፣ ኤለን መስክና ሰር ሪቻርድ ይጠቀሳሉ፡፡ በሩሲያ በኩልም ይኸው ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ መሰናዶ እንዳለ ተነግሯል፡፡

ቢሊየነሩ ኤለን መስክ ለሰር ሪቻርድ የሙከራ ጉዞ ድጋፍ ለመስጠት ኒው ሜክሲኮ ድረስ ሄዶ የሮኬቷን መመንጠቅ ቅጽበት በአካል ተከታትሏል፡፡

ጠፈር ከየት ነው የሚጀምረው የሚለው ጉዳይ ዛሬም ድረስ እያከራከረ ሲሆን ናሳ ከባሕር ጠለል በላይ 80 ኪሎ ሜትር ላለፈ የውስጠኛውን ከባቢ ሕዋ ድንበር ተሸግሯል የሚል እውቅና ይሰጣል፡፡

በጠፈር ቱሪዝም ከሚሳተፉ ኩባንያዎች መካከል ብሉ ኦሪጅን ኩባንያን የሚያስተዳድረው ቢሊየነሩ ጄፍ ቤዞስ ግን ጠፈር ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ ነው የሚጀምረው ሲል የሰር ሪቻርድን ጉዞ እውቅና ለመስጠት እያቅማማ ነው፡፡

በዓለም ላይ ከ80 ኪሎ ሜትር ሽቅብ የሕዋ ድንበር ያለፉ የሰው ልጆች ቁጥር በድምሩ 580 ብቻ ናቸው፡፡