ትናንት ፍጹም ቅጣት ምት በሳቱት ጥቁር እንግሊዛውያን ላይ የዘረኝነት ጥቃት ደርሷል ተባለ

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, Carl Recine - Pool

የምስሉ መግለጫ, ቡካዮ ሳካ ፍጹም ቅጣት ምት ከሳተ በኋላ
ታትሟል

ትናንት ጣሊያን እንግሊዝን በፍጹም ቅጣት ምት አሸንፋ ሻምፒዮን ስትሆን ሦስት ፍጹም ቅጣት ምት በሳቱት ጥቁር እንግሊዛውያን ላይ የዘረኝነት ጥቃት መድረሱ ተነገረ።

ጣሊያ እና እንግሊዝ በመደበኛው እና በተጨማሪ ሰዓት 1ለ1 በማጠናቀቃቸው አሸናፊውን ለመለየት ቡድኖቹ ወደ መለያ ምት ተሸጋግረው ነበር።

ይሁን እንጂ ማርከስ ራሽፎርድ የመታት ፍጹም ቅጣት ምት በግቡ ብረት ሲመለስ ጄደን ሳንቾ እና ቡካዮ ሳካ የመቷቸው ኳሶች በጣሊያናዊው ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ዶናሩማ ተመልሰዋል።

ይህን ተከትሎ በሦስቱ ተጫዋቾች ላይ በማህበራዊ ድር አምባ የዘረኝነት ጥቃት ደርሶባቸዋል።

በጉዳዩ ላይ የእንግሊዝ እገር ኳስ ማህበር ያተገቢ ያልሆነ ሲል ፖሊስ ደግሞ ምርመራ ጀምሬያለሁ ብሏል።

line

እንግሊዝ ለትልቅ ክብር ለመብቃት ከ55 ዓመት በላይ ያደረገች ጥበቃ ሳይሳካለት ቀርቷል።

የማንቸስትር ዩናይትዱ ሉክ ሾው በሁለተኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል እንግሊዝ ባለ ክብር ለመሆን በትክክለኛው መንገድ ላይ እንደሆነች አስመስሎ ነበር።

በ33 ጨዋታዎች ያልተሸነፈችው ጣሊያን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ በ67ኛው ደቂቃ በተከላካዩ ሊዮናርዶ ቦኑቺ ጎል አቻ ለመሆን በቃች።

ጨዋተው ወደ ተጨማሪ ሰዓት ቢያመራም ጎል መቆጠር ሳይችል ቀርቷል።

ጨዋተው በፍጹም ቅጣት ምት ሲጠናቀቅ ሦስት እንግሊዝ ተጨቻዋቾች ዕድሎቻቸውን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

አምበሉ ሃሪ ኬን እና ተከላካዪ ሃሪ ማጓየር ከፍጹም ቅጣት ምት ማስቆጠር የቻሉ የእንግሊዝ ተጫዋቾች ናቸው።

የእንግሊዙ ግብ ጠባቂ ፒክፎርድ በበኩሉ የአንድሪያ ቤሎቲ እና የጆርጂንሆን ኳሶች በማዳን የቡድኑን ተስፋ ማለምለም ችሎ ነበር።

ዶሜኒኮ ቤራዲ፣ ሊዮናርዶ ቦኑቺ እና ፌደሪኮ በርናርዴስኪ ደግሞ ፍጹም ቅጣት ምቱን ወደ ጎልነት የቀየሩ ተጫዋቾች ናቸው።

ራሽፎርድ እና ሳንቾ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ተቀይረው የገቡ ሲሆን የአንግሊዙ አሰልጠኝ ጋሬት ሳውዝጌት ለፍጹም ቅጣት ምት ብለው ቀይረው እንዳስገቧቸው ቢገመትም ሳይሳካለቸው ቀርቷል።

ጣሊያኖችም ያለመሸነፍ ክብራቸው ወደ 34 ጨዋታዎች ባሳደጉበት ምሽት የዩሮ 2020 ክብርን ለመጎናጸፍ በቅተዋል።

አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ በዕድሜ የገፉ ተጫዋቾችን ከወጣቶች ጋር በማቀናጀት ምርጥ የሚባል ውድድር ለማሳለፍ ችለዋል።

ቡድናቸው በውድድሩ ላይ እንደ ቤልጂም እና ስፔን ያሉ ቡድኖችን በማሸነፍ ነው ለፍጻሜ የበቃው።

ለ2018ቱ የሩሲያ የዓለም ዋንጫ ማለፍ ተስኗት ለነበረችው ጣሊያን ድሉ የማንቺኒ እና የቡድኑ ጠንካራ ሥራ ውጤት ተደርጎ ተወስዷል።

ጣሊያን በትላንት ምሽቱ ጨዋታ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በጎል ሙከራ ከእንግሊዝ የተሻለች ሆና አምሽታለች።

የጣሊያን ቡድን ከድል በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"ሽንፈቱ የሚያሳምም ነው"

ሽንፈቱን "የሚያሳምም"? ያሉት አሰልጣኝ ሳውዝጌት ተጫዋቾቻቸው "ማድረግ የሚችሉትን በሙሉ ማድረጋቸውን" ተናግረዋል።

"ሁላችንም በህብረት ቆመን ነበር። ተጫዋቾቹ ለሃገራቸው የማይታመን አስደሳች ጊዜን ሰጥተው ነበር" ብለዋል።

የ22 ዓመቱ ጣሊያናዊው ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ዶናሩማ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል።

ስፔናዊው የ18 ዓመቱ አማካይ ፕድሪ የውድድሩ ወጣት ኮከብ ተጫዋች ለመባል በቅቷል።

ፑርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአምስት ጎሎች እና አንድ ለጎል አመቻችቶ ኳስ በማቀበሉ የውድድሩ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ አጠናቋል።