ደቡብ አፍሪካ የጉፕታ ቤተሰቦችን ለመያዝ የኢንተርፖልን ድጋፍ ጠየቀች

ታትሟል

ደቡብ አፍሪካ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የሚጠረጠሩ የጉፕታ ቤተሰብ አባላትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የኢንተርፖልን ድጋፍ ጠየቀች።

የዚህ ቤተሰብ አባላት የተጠረጠሩበትን የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል የተባለው በፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማ አስተዳደር ወቅት ነው።

የጉፕታ ቤተሰብ አባላት በደቡብ አፍሪካ ያላቸውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ እና የተሻለ ትርፍ ለማግኘት ለመንግሥት ባለሥልጣናት ጉቦ ይሰጡ ነበር ተብሏል።

የቤተሰብ አባላቱ ግን ምንም ጥፋት አልሰራንም ይላሉ።

ደቡብ አፍሪካ፤ ኢንተርፖል አቱል ጉፕታ እና ባለቤቱን ቼታሊ እንዲሁም ራጄሽ ጉፕታ እና ባለቤቱን አርቲ በቁጥጥር ሥር እንዲያውልላት ጠይቃለች።

ዓለም አቀፍ የወንጀል ፖሊስ ድርጅት ወይም ኢንተርፖል በሚለው ስሙ የሚታወቀው ድርጅት ዋና መቀመጫውን ፈረንሳይ ሊዮን ያደረገ ሲሆን፤ በመላው ዓለም ወንጀልን ለመቆጣጠር ጥናፋተኞችን አድኖ ለመያዝ የፖሊስ ኃይሎችን ያስተባብራል።

የጉፕታ ቤተሰብ አባላት በአሁኑ ወቅት በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እንደሚኖሩ ይነገራል።

የደቡብ አፍሪካ ዐቃቤ ሕግ ከደቡብ አፍሪካ ውጪ የሚገኙ የጉፕታ ቤተሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልከው ለሕግ እንዲቀርቡ ኢንተርፖልን ጠይቋል።

የቤተሰብ አባላቱ የሙስና ክስ የቀረበባቸው 25 ሚሊዮን ራንድ ወጪ የሆነበት የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አዋጭነት ጥናት ላይ ወጪ በተደረገ ገንዘብ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ማስመስል እና የማጭበርበር ወንጀል ክሶችም ቀርቦባቸዋል።