ለትራምፕ የድንበር ላይ አጥር ፕሬዝዳንት ባይደን በጀት ከለከሉ

ታትሟል

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ ትራምፕ ላስጀምሩት የድንበር ላይ የግንብ አጥር በጀት ከለከሉ።

ዶናልድ ትራምፕ አስጀምረውት ለነበረው የድንበር ላይ አጥርን ለመገንባት የሚውል በጀት የብሔራዊ ድንገተኛ አደጋ የበጀተውን ገንዘብ እንዲያቆም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ትናንት ለኮንግረሱ በጻፉት ደብዳቤ ግንባታውን "ዋስትና የሌለው" ያሉት ሲሆን ከታክስ የተሰበሰበ ማንኛውም ገንዘብ ለዚህ ረብ የለሽ ነገር መዋል የለበትም ብለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ለአጥሩ ግንባታ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት የኮንግረሱ ፍቃድ እንዳያስፈልጋቸው እአአ 2019 ላይ በአሜሪካ ደቡባዊ ግዛት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀው ነበር።

ይህን ተከትሎም ትራምፕ ለአጥሩ ግንባታ ከአሜሪካ ጦር በጀት ሲወስዱ ነበር።

ትራምፕ ከዋይት ሐውስ እስከተሰናበቱበት ጊዜ ድረስም ለግንባተው ቢያንስ 25 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ተደርጓል።

ትናንት ይህ ፕሮጀከት እንዲቋረጥ ትዕዛዝ የሰጡት ፕሬዝዳንት ባይደን በቀድሞው አስተዳደር ያለአግባብ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል ያሏቸውን ሌሎች ውሳኔዎችንም ሽረዋል።

የስደተኞች ፖሊሲን በመከለስ ባለፈው ሳምንት በትራምፕ የስደተኞች ፖሊሲ ምክንያት ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦችን እንደገና እንዲገናኙ አድርገዋል።

ትናንት ፕሬዝዳንት ባይደን የድንበር ላይ ግንባታው እንዲቋረጥ ባዘዙበት ደብዳቤ፤ ለግንባታው ገንዘብ እንዴት ወጪ ሲሆን እንደነበር ማብራሪያ እፈልጋለሁ ብለዋል።

የድንበር አጥሩን መገንባት ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ዋነኛ አጀንዳቸው ነበር።

ይሁንና በዲሞክራቶች የተሞላው ኮንግረስ ፕሬዝዳንቱን ይሁንታ ስላልሰጣቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ግንባታውን አስጀምረዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመደበኛው አካሄድ የማይወሰኑ ጉዳዮች ላይ ብቸኛ ሚና እንዲኖረው እና የአገሪቱን ጦር በጀት እንዲጠቀሙ ፍቃድ ይሰጣል።

ትራምፕ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት ግንባታቸው የተለያዩ ከ1 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝሙ የድንበር ላይ አጥሮች ነበሩ።

በእሳቸው ዘመን ተጨማሪ 129 ኪ/ሜ አካባቢ በአዲስ የተሰራ ሲሆን 647 ኪ/ሜ አካባቢ የሚሆነው ደግሞ እንደገና ተቀይሯል።

የአሪዞና የኮንግረስ ተወካይ ራውል ግሪቫልቫ "የትራምፕ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለብሔራዊ ደኅንነት ፋይዳ የለውም" በማለት ሞግተው የነበረ ሲሆን የፕሬዝዳንት ባይደንን ትዕዛዝ ተከትሎ "አሁን ኮንትራቱን አቋርጠን ሌላ ግንባታ እንዳይካሄድ ማድረግ አለብን" ብለዋል።

በሌላ በኩል የቀድሞው የዶናልድ ትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ አማካሪ ጃሰን ሚለር የፕሬዝዳንቱን ደብዳቤ ተከትሎ በትዊተር ገጻቸው አጭር አሽሙር መሳይ መልዕክት አስፍረዋል። "ባይደን በሕገ ወጥ ስደተኞች ፍቅር ተነድፈዋል" የሚል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተወሰኑት የትራምፕ ስደተኞችን የተመለከቱ ፖሊሲዎች ግን በቦታቸው ይቆያሉ ተብሏል።

ለምሳሌ የድንበር አካባቢ ሹማምንት ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን ከድንበር የማስወጣት ስልጣን ባለበት ይቀጥላል ተብሏል።

ይህም በኮሮናቫይረስ ምክንያት እንደ አዲስ ሰነድ የማሰራት ሂደቱ ለኮሮናቫይረስ ስርጭት አስቸጋሪ በመሆኑ አሁን ጊዜው ስላልሆነ ክልከላው እንደሚቀጥል የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።