የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሚኒስትሮቻቸው በምሽት ክበቦች በመገኘታቸው ይቅርታ ጠየቁ

ታትሟል

በጃፓን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት የወጣውን መመሪያ ተላልፈው ወደ ምሽት ክበቦች የሄዱ የአገሪቱ ባለስልጣናት ጉዳይ ከፍተኛ ትችትን አስከትሏል።

ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሚኒስትሮቻቸው ስም ለህዝቡ ይቅርታ ለመጠየቅ ተገደዋል።

መንግሥት በተደጋጋሚ አላስፈላጊ የሆኑ ስብሰባዎችን ህዝቡ እንዲያስወግድ ሲናገር የነበረ ሲሆን ይህንንም ሁኔታ ሚኒስትሮቹ አለማክበራቸው አወዛጋቢ ሆኗል።

"ዜጎቻችንን ከምሽት ሁለት ሰዓት በኋላ ወደ ሬስቶራንቶች ወጥታችሁ አንዳትበሉ እንዲሁም አላስፈላጊ የሆኑና አስቸኳይ ካልሆነ ከቤታችሁ አትውጡ በምንልበት ወቅት ይህ በመፈጠሩ በጣም አዝኛለሁ" በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሺሂዴ ሱጋ በዛሬው እለት ለፓርላማው አስረድተዋል።

የጃፓን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ሪፖርት ባደረጉት መሰረት አንደኛው ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት የጣልያን ሬስቶራንት ውስጥ እራት ከበሉ በኋላ ሞቅ ደመቅ ባለው የመዲናዋ ቶክዮ ማዕከል በሆነው ጊንዛ ወደሚገኙ ሁለት የምሽት ክበቦች አምርተው ነበር ብለዋል።

እንዲሁ ሌላኛው ሚኒስትር ጊንዛ በሚገኝ ታዋቂ ክለብ በተደጋጋሚ መሄዳቸውን የአገሪቱ ሚዲያ አስነብቧል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝ ለሁለተኛ ዙር እያገረሸ ባለባት ቶክዮ ባለስልጣናቱ የአስቸኳይ ጊዜ አውጀዋል።

በጃፓን ከ370 ሺህ በላይ ዜጎቿ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን ከ5 ሺህ በላይ ዜጎቿንም አጥታለች።