ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኡጋንዳዊው ተቃዋሚ ቦቢ ዋይን ከቁም እስር እንዲወጣ ትዕዛዝ ተሰጠ
የኡጋንዳ ፍርድ ቤት ተቃዋሚው ቦቢ ዋይን ከቁም እስር እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ሰጠ።
የቦቢ ዋይንን ቤት የከበቡት ፖሊሶችና መከላከያ ኃይል እንዲነሳ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
ከ11 ቀናት በፊት ብሔራዊ ምርጫ ከተካሄደበት ቀን አንስቶ ቦቢ ዋይን ከቤቱ እንዳይወጣ ታግዶ ነበር።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሰጠው የተቃዋሚው ጠበቆች ፊርማ አሰባስበው ቅሬታ ማሰማታቸውን ተከትሎ ነው።
መንግሥት እገዳውን የጣለው ቦቢ ዋይን ተቃውሞ እንዳያነሳሳ ነው ብሏል።
ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ ተቃዋሚው ላይ የተጣለው እገዳ ሕገ ወጥና ሰብአዊ ነጻነቱን የሚጋፋ ነው ብሏል።
ዩዌሪ ሙሴቪኒ ያሸነፉበት ምርጫ ቅስቀሳ ሲካሄድ ብዙ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸው አይዘነጋም።
ተቃዋሚው በምርጫው 35 በመቶ ድምጽ ያገኘ ሲሆን፤ ብሔራዊ ምርጫው ተጭበርብሯል ብሏል።
የኡጋንዳ የምርጫ ኮሚሽን በበኩሉ ምርጫው ሰላማዊ ነበር ይላል።
የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ሕብረትና የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ምርጫው ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
ምርጫውን መታዘብ የቻለው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ብቻ ነበር።
ቦቢ ዋይን ከምርጫው በኋላ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ "ለእኔና ለባለቤቴ ሕይወት እሰጋለሁ" ብሎ ነበር።
የጸጥታ ኃይሎች የቦቢ ዋይንን ቤት ከበው ማንንም አያስገቡም፣ አያስወጡምም ነበር።
የመከላከያው ቃል አቀባይ ብ/ር ፍላቫ ባይኮሶ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንደሚያከብሩ ተናግረዋል።
የጸጥታ ኃይሎች እንደታዘዙት ከቦቢ ዋይን ቤት ቢነሱም እንኳን ስለ ምርጫው ውጤት ቅሬታ ለማቅረብ የቀሩት አራት ቀናት ብቻ ናቸው።
ቅሬታውን ለፍርድ ቤት ካቀረበ ፍርድ ቤት በ45 ቀናት ውስጥ ውሳኔውን ያስታውቃል።
የቦቢ ዋይን ፓርቲ ናሽናል ዩኒቲ ፕላትፎርም ከመሪያቸው ከቦቢ ጋር መገናኘት ሳይችሉ በመቆየታቸው ቀጣይ እርምጃቸው ምን እንደሆነ በግልጽ እንዳላወቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፈው አርብ በፌስቡክ ቀጥታ በተላለፈ መልዕክቱ፤ ኡጋንዳውያን ተቃውሞ የማሰማት መብት አላቸው ሲል ቦቢ ዋይን ተደምጧል።