ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቶክዮ ኦሎምፒክ በዝግ ሊካሄድ እንደሚችል ተጠቆመ
በጃፓን፣ ቶክዮ የሚካሄደው የዘንድሮው ኦሎምፒክ በዝግ ሊከናወን እንደሚችል ተገለጸ።
የዓለም አትሌቲክስ ኃላፊው ሎርድ ኮ እንዳሉት፤ ውድድሩ ዘንድሮ የሚካሄድ ከሆነ በዝግ ሊከናወን ይችላል።
ታይምስ የአትሌቲክስ እና ፓራኦሎምፒክስ ውድድሮች ሊሰረዛሉ ይችላሉ ቢልም፤ ኃላፊው ውድድሮቹ እንደሚካሄዱ አረጋግጠዋል።
"ደጋፊዎች በሐሴት እየጮሁ ውድድሩን በፍቅር ቢከታተሉ ደስ ይለኝ ነበር። ግን ውድድሩ በዝግ ቢሆንም ሰው ይረዳናል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።
እአአ 2010 ላይ በለንደን የተካሄደውን ኦሎምፒክ የመሩት ኃላፊው፤ ውድድሩን መሰረዝ "አዋጭ መፍትሔ አይሆንም" ሲሉ ገልጸዋል።
ውድድሩን መግፋት በ2024 በፓሪስ፣ በ2028 በሎስ አንጀለስ የሚካሄዱት ኦሎምፒኮች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አያይዘው ጠቅሰዋል።
አምና ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የቶክዮ ኦሎምፒክ በወረርሽኙ ሳቢያ በዓመት ተገፍቶ ወደ ዘንድሮ ተሸጋግሯል።
ሆኖም ግን ጃፓንን ጨምሮ በሌሎችም አገሮች ወረርሽኙ እያገረሸ መምጣቱ ውድድሩን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።
ታይምስ አንድ የጃፓን ገዢ ፓርቲ አባልን ጠቅሶ ባለፈው ሳምንት ያወጣው ዘገባ፤ ውድድሩ ሊሰረዝ እንደሚችል አትቷል።
ዘገባው ከወጣ በኋላ የቶክዮ 2020 አዘጋጆች የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ዮሾንዴ ሱጋ "ውድድሩን ለማካሄድ ቆርጠን ተነስተናል" ማለታቸውን ተናግረዋል።
የቶክዮ ኦሎምፒክ በተያዘለት ጊዜ ሰሌዳ እንደሚካሄድ አስረግጦ የተናገረው የጃፓን መንግሥት፤ ታይምስ ስለ ውድድሩ መሰረዝ ያወጣውን ዘገባ አጣጥሏል።
የቶክዮ አገረ ገዢ ዩሮኮ ኮይኬ ታይምስ ላይ ቅሬታ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
በእርግጥ የቶክዮ ኦሎምፒክ በታቀደለት ጊዜ ላይከናወን ይችላል ያለው ታይምስ ብቻ አይደለም። ተመሳሳይ ጥያቄዎች ከተለያየ አቅጣጫ ተሰንዝረዋል።
ውድድሩ እንደተባለው ከተካሄደ፤ ኦሎምፒክ ሐምሌ 23፣ ፓራሊምፒክስ ደግሞ ነሐሴ 24 ይጀመራሉ።
የቶክዮ 2020 ዋና ኃላፊ ቲሺሮ ሙቶ እንዳሉት፤ ለኮሮናቫይረስ ክትባት መገኘቱ ውድድሩ እንዲካሄድ አበረታቷል።
"ክትባት በአሜሪካ እና በአውሮፓ በስፋት ከተሰራጨ በኋላ ስጋት አይኖርብንም። ይህ ብቻ በቂ ነው ባንልም ትልቁ ተስፋችን የክትባቱ መሰራጨት ነው" ብለዋል።
የዓለም አትሌቲክስ ኃላፊው ሎርድ ኮም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።
"አምና ከነበረው ሁኔታ የዘንድሮው የተለየ ነው። ውድድሩ ገና ስድስት ወራት ይቀረዋል። እስከዛድረስ ክትባት በስፋት ይሰጣል" በማለት አብራርተዋል።