ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሥነ ልቦና አማካሪ ጋር የተወራ ሚስጥርን ለማጋለጥ የሚያስፈራሩት መዝባሪዎች
ፊንላንድ ውስጥ የሥነ ልቦና ምክር የሚወስዱ ሰዎች ለሀኪማቸው የተናገሩት ሚስጥር እየተሰረቀ ነው። የኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች ይህን ሚስጥር ሰርቀው፤ ገንዘብ ካልተከፈላቸው ሚስጥሩን አደባባይ እንደሚያወጡት ያስፈራራሉ።
በፊንላንድ የሚገኝ ትልቅ የሥነ ልቦና አማካሪ ክሊኒክ ውስጥ ህክምና ይከታተሉ የነበሩ ሰዎች ግላዊ መረጃ ተመዝብሯል።
ቫስታሞ የተባለው ክሊኒክ ከ20 በላይ ቅርንጫፎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ታካሚዎች አሉት። የግል መረጃቸው የተመዘበረባቸው ሰዎች ለፖሊስ እንዲያስታውቁም ክሊኒኩ አሳስቧል።
የክሊኒኩ የመረጃ ቋት የተመዘበረው በጎሮጎሳውያኑ በኅዳር 2018 እና በሚያዝያ 2019 እንደሆነ ይገመታል።
"መረጃ መዝባሪዎቹ ሀፍረተ ቢስ ናቸው"
ክሊኒኩ ከፖሊስ ጋር ተባብሮ እየሠራ እንደሆነ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አሁን ላይ የመገናኛ ብዙኃን ክፍሉ የኢሜል አድራሻ አይሠራም።
እስካሁን የ300 ታካሚዎች ግላዊ መረጃ ተሰርቆ በስውሩ ድረ ገጽ 'ዳርክ ዌብ' መታተሙን አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ክሊኒኩ የታካሚዎች መረጃ መመዝበሩ "ከባድ ቀውስ ነው" ብሏል።
ቫስታሞ፤ ታካሚዎች እርዳታ የሚያገኙበት ነጻ የስልክ መስመር ከፍቷል።
ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች አንድ ነጻ የምክር አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፤ የምክር አገልግሎቱ እንደማይቀረጽ አስታውቋል።
የፊንላንድ መንግሥት ባለፈው እሑድ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል። የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ማርያ ኦሳሎ "ልዩ ሁኔታ ነው" ብለዋል።
የበይነ መረብ ደህንነት ድርጅት የሆነው ኤፍ-ሰክዩር ሠራተኛ ሚኮ ሀፖነን "መረጃ መዝባሪዎቹ ሀፍረተ ቢስ ናቸው። አንዳንዶቹ ታካሚዎች 18 ዓመት እንኳን አልሞላቸውም" ሲል ተናግሯል።።
ግላዊ መረጃቸው ከተሰረቀባቸው አንዱ የሆነው ጄሪ ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ 'ዘ ራንሰም ጋይ' በሚል ራሱን የሚጠራ ሰው በቢትኮይን (ዲጂታል ገንዘብ) ጉቦ እንዲከፍል ጠይቆታል።
መጀመሪያ ላይ የተጠየቀው 40 ዩሮ ቢሆንም፤ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ስላልከፈለ 200 ከዛም 500 ዩሮ ክፈል ተብሏል።
ክፍያውን ካልፈጸመ ግን ወጣት ሳለ ከሥነ ልቦና ሀኪም ጋር ያደረገው ንግግር ይፋ እንደሚወጣም ተነግሮታል።
"ከሥነ ልቦና አማካሪዬ ያደረግኳቸው ንግግሮችን የያዘ ጽሑፍ በመረጃ መዝባሪዎች እጅ መግባቱ አስጨንቆኛል" ብሏል ጄሪ።
አያይዞም "በጽሑፍ የተቀመጡትን ነገሮች ከተቀረው ዓለም ጋር ለመጋራት ዝግጁ አይደለሁም" ሲል ስሜቱን ገልጿል።
ከሀኪሙ ጋር ያወራው ነገር በማስታወሻ ደብተር ላይ ነበር የተጻፈው። ጽሑፉ ወደ ኮምፒውተር እንደሚሸጋገር አልተነገረውም ነበር።
መረጃ መዝባሪው እንዲከፍል ያዘዘውን ገንዘብ የመክፈል አቅም እንደሌለው የሚናገረው ጄሪ፤ "ብከፍልም እንኳን የግል መረጃዬ አደባባይ እንደማይወጣ ማረጋገጫ የለኝም" ብሏል።
መረጃቸው የተጋለጠባቸው 300 ሰዎች እጣ ፈንታ ይደርሰኛል ብሎ ይሰጋል። ግላዊ መረጃቸው ከመነበቡ ባሻገር ለማንነት ስርቆት ሊጋለጡ እንደሚችሉም ስጋት አለ።