ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፓኪስታን ትምህርት ቤት በደረሰ ጥቃት ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሞቱ
በፓኪስታን ትምህርት ቤት ውስጥ በደረሰ ፍንዳታ ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሲሞቱ፤ 50 ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በሃይማኖት ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች እየተማሩ ሳለ ነበር ጥቃት የተሰነዘረው።
የሆስፒታል ምንጮች እንዳሉት፤ በጥቃቱ የሞቱት ከ20 እስከ 30 እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው። ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አራቱ ከ13 ዓመት በታች ያሉ ልጆች ናቸው።
እስካሁን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም። ምርመራ እየተካሄደም ነው።
የምርመራው የመጀመሪያ ዙር ውጤት እንደሚያሳየው፤ ከሞቱት አራቱ ሕጻናት ናቸው።
በአፍጋኒስታን ድንበር ላይ የምትገኘው ፐሽዋር ከተማ፤ በታሊባን ሰርጎ ገቦች ከፍተኛ ጥቃት ከተሰነዘረባቸው ግዛቶች አንዷ ናት።
ከስድስት ዓመታት በፊት ታጣቂዎች ወታደራዊ ትምህርት ቤት ወረው ታዳጊዎችን ጨምሮ ከ150 በላይ ሰዎች ገድለዋል።
ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጥቃቶች ቀንሰው ነበር።
ማዳራሳ የተባለው የሃይማኖት ትምህርት ቤቱ ላይ ጥቃት የተሰነዘረው ወደ 60 የሚጠጉ ተማሪዎች እየተማሩ ሳለ ነበር።
አንድ ግለሰብ በሻንጣ ተቀጣጣይ ይዞ ወደ ሕንጻው ሲገባ ማየታቸውን አንድ የዐይን እማኝ ለፖሊስ ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ከምስሎች መረዳት ተችሏል።
ተባባሪ ኢንስፔክተር ሻፋቅ ማሊክ ለፓኪስታን መገናኛ ብዙኃን እንዳሉት፤ ጥቃቱ የደረሰው በ5 ኪሎ ግራም ተቀጣጣይ ነው።
የሆስፒታል ሠራተኞች ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ በብዛት የእሳት ቃጠሎ የደረሰባቸው ሰዎች ተቀብለዋል።
ኤኤፍፒ ፖሊስን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ጉዳት ከደረሰባቸው ሁለቱ መምህራን ናቸው።
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራን ከሀን ጥቃቱን እጅግ አውግዘው "ስለጠፋው ሕይወት አዝናለሁ" ብለዋል።