ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሴቶች 'በአስነዋሪ' ሁኔታ ስለመፈተሻቸው አውስትራሊያ ከኳታር ማብራሪያ ጠየቀች
ከዶሀ ወደ ሲድኒ በረራ ከመካሄዱ አስቀድሞ ሴቶች ለፍተሻ ልብሳቸውን እንዲያወልቁ መደረጉን የአውስትራሊያ መንግሥት አስታወቀ።
'በጣም አስነዋሪ' ያለውን ፍተሻ በተመለከተም የአውስትራሊያ መንግሥት ከኳታር ማብራሪያ ጠይቋል።
ሃማድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ በሚገኝ መጸዳጃ ቤት ጨቅላ ልጅ መገኘቱን ተከትሎ ነበር ፍተሻው የተካሄደው። የጨቅላው ማንነት እስካሁን አልታወቀም።
የዓይን እማኞች ለአውስትራሊያ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፤ ሴት ተሳፋሪዎች ከኳታር ኤር ዌይስ አውሮፕላን እንዲወርዱ ተደርጓል። ሴቶቹ በቅርቡ ልጅ ስለመውለዳቸው የሚያመላክት ምልክት ሲፈለግባቸው ነበር ተብሏል።
13 አውስትራሊያውያን ሴቶች ወደ አምቡላንስ ተወስደው ለምርመራ የውስጥ ሱሪያቸውን እንዲያወልቁ ተነግሯቸዋል።
ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ከተደረጉት አንዷ ኪም ሚልስ ለጋርዲያን እንደተናገሩት፤ ወደጨለማ የመኪና ማቆሚያ ተወስደዋል። በቦታው ሦስት አምቡላንሶች ለሴቶቹ ምርመራ ለማድረግ እየጠበቁ ነበር።
በ60ዎቹ እድሜ ክልል የሚገኙት ኪም ሳይመረመሩ መቅረታቸውንም አስረድተዋል። ባይመረመሩም ግን ያዩት ነገር አስቀያሚ እንደነበር አክለዋል።
"እግሬ እየተንቀጠቀጠ ነበር። የሆነ ቦታ ይወስዱኛል ብዬ ፈርቼ ነበር። ምን እየተካሄደ እንደነበር ለምን አልነገሩንም? በጣም አሰቃቂ ነበር። ወጣቶቹ ሴቶች ምን እንደተሰማቸው ማሰብ ይከብደኛል" ብለዋል።
ከተሳፋሪዎቹ አንዱ ዎልፍጋንግ ባቤክ ለአውስትራሊያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንደተናገረው፤ ሴቶቹ በጣም ተቆጥተው ወደ አውሮፕላኑ ተመልሰዋል።
"ብዙዎቹ በጣም ተበሳጭተው ነበር። አንድ ወጣት ሴት እያለቀሰች ነበር" ብሏል።
ጥቅምት 2 የተከሰተውን ፍተሻ በተመለከከተ የኳታር መንግሥት ገና ምላሽ አልሰጠም።
"የሚረብሽ፣ ክብረ ነክ እና አሳሳቢ"
የአውስትራሊያ መንግሥት እንዳለው፤ ሁኔታው ሴቶቹ ፍቃዳቸውን የሚሰጡበት አልነበረም።
የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማሪስ ፔኒ "የሚረብሽ፣ ክብረ ነክ እና አሳሳቢ" ያሉትን ፍተሻ ለአውስትራሊያ ፌደራል ፖሊስ እንዳሳወቁና ከኳታር ማብራሪያ ካገኙ በኋላ ቀጣዩ እርምጃ ምን መሆን እንዳለበት እንደሚወስኑ ተናግረዋል።
የሀማድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቃል አቀባይ፤ "የህክምና ባለሙያዎች ልጅ ስለወለደች እናት ጤናና ደህንነት ጉዳይ እንደሰጉና አውሮፕላኑ ከመብረሩ በፊት ማንነቷ መታወቅ እንዳለበት ገልጸዋል። ጨቅላ ልጅ የተገኘበት የአየር ማረፊያው አካባቢ የነበሩ ሰዎች ትብብር እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል" ብለዋል።
ልጁ በማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪዎችና በሀኪሞች እንክብካቤ እየተደረገለት ሲሆን፤ አየር ማረፊያ ስለ እናቲቱ መረጃ ጠይቋል።